የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሰሩ መፈቀዱ የፋይናንስ ተወዳዳሪነትን በማነቃቃት የዘርፉን ተደራሽነት ይጨምራል-ኤርሚያስ አመልጋ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሰሩ መፈቀዱ የፋይናንስ ተወዳዳሪነትን በማነቃቃት የዘርፉን ተደራሽነት ይጨምራል-ኤርሚያስ አመልጋ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሰሩ መፈቀዱ የፋይናንስ ተወዳዳሪነትን በማነቃቃት ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል መድረስ የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር የኢኮኖሚ ባለሙያው ኤርሚያስ አመልጋ ገለጹ።
በኢትዮጵያ በ1901 ዓ.ም የባንክ አገልግሎት መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
እስከ 1970ዎቹ ድረስ የጣሊያንና የህንድን ጨምሮ የሌሎች አገራት ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ ትከተለው በነበረው ርዕዮተ ዓለም ምክንያት የውጭ አገራት ዜጎች ባንኮቻቸውን ዘግተው ወደ አገራቸው ለመመለስ ተገደዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ አካላት ዝግ እንደሆነ ቆይቷል።
የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያው ኤርሚያስ አመልጋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ለውጭ ባንኮች ዝግ ሆኖ መቆየቱ የፋይናንስ ስርዓቱ እና የምንዛሬ ግብይቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት የውጭ አገራት ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የተከፈተው እድልም እንደ አዲስ ሊታይ እንደማይገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዘግይታም ቢሆን ወደነበረችበት የፋይናንስ አሳታፊ ስርዓት መመለሷ በቴክኖሎጂ፣ በዓለም አቀፍ ንግድና በፋይናንስ መሰረተ ልማት ዕድገት ላይ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከስራ ዕድል ባለፈ የተሻለ የፋይናንስ ተወዳዳሪነትን ይፈጥራል ብለዋል።
በዘርፉ የሚፈጠረው የፋይናንስ ውድድርም አዳዲስ አገልግሎቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ በማድረግ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የፋይናንሰ ስርዓት በመፍጠር የባንክ ዘርፉ እንዲነቃቃ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የውጭ አገራት ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡም አዳዲስ ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ የአገር ውስጥ ባንኮች ያልደረሱበትን ዘርፍ በመሙላት ተደራሽነትን እንደሚያሳድጉ ጠቅሰዋል።
ይህም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የውጭ ባንኮች የገንዘብ፣ የእውቀት፣ እና የቴክኖሎጂ ተወዳደሪነት አቅምን ይዘው ስለሚመጡም የገበያ ክፍተትን ለመሙላት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ባንኮች የብድር ተደራሽነት ውስን መሆኑን ጠቅሰው፤ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ መሳተፋቸው ይህንን ክፍተት በመሙላት ረገድ የተሻለ ስራ እንደሚሰሩ ያላቸውን አምነት ገልጸዋል፡፡
የውጭ አገራት ባንኮች ወደ ገበያው ይዘውት የሚገቡት የፋይናንስ አቅም የአገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ከፍተኛ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮችም በገበያው ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል ከአገር ውስጥ ባለፈ በሌሎች አገራት ኢንቨስት ማድረግ የሚያስቻለቸውን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት አቅም ማጎልበት እንዳለባቸው መክረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የባንክ ኢንዱስትሪውን ፍትሃዊ በሆነ የአገልግሎት ስርዓት ለመምራት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መንግሥት የውጭ አገራት ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ገብተው መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን ይሁንታ መስጠቱ ይታወቃል።