የሰላም ስምምነቱ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍታት የሚለውን የኢትዮጵያን አቋም እውን ያደረገ ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍታት የሚለውን የኢትዮጵያን አቋም እውን ያደረገ ነው - ምሁራን
አዳማ ሕዳር 01 ቀን 2015 (ኢዜአ) --የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት ስታራምድ የቆየችውን አቋም እውን ያደረገ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ እንዲያገኙ የተለያየ ሙከራ ስታደረግ ቆይታለች።
ከምሁራኑ መካከል ዶክተር ዘለቀ ተመስገን፤ "ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ማግኘት አለባቸው የሚለውን ሃሳብ ለረዥም ጊዜ ስታስተጋባና ስታራምድ የቆየች አገር ናት" ሲሉ አስታውቀዋል።
በፌዴራል መንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትም ኢትዮጵያ ቀድማ ስታራምድ የነበረውን አቋሟን እውን ያደረገ ነው ብለዋል ዶክተር ዘለቀ።
ስምምነቱ ከንግግር ባለፈ "አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር መፍታት ይችላሉ" የሚለውን ሃሳብና አቋም በተግባር ያሳየ መሆኑንም ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ከቀድሞውኑም በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና ስትጫወት እንደነበረ ያስታወሱት ዶክተር ዘለቀ፤ የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ስር በነበሩበት ጊዜም አገሮቹ ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ የተለያየ እንቅስቃሴ ስታደርግና ስትደግፍም ነበር ብለዋል።
ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን የተገኘውን የሰላም ዕድል ተጠቅመው ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ለማሳካት መትጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል ዶክተር ዘለቀ።
በተጨማሪም የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በውስጥም በውጪም ያሉ ኢትዮጵያውያን ተሳትፏቸው የጎላ መሆን አለበት ብለዋል።
ምሁራንም የኢትዮጵያ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ሙያና እውቀታቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው ነው ያሉት ዶክተሩ።
የሰላም ስምምነቱ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት መደረጉ ለአፍሪካ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የገለፁት ደግሞ ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ ናቸው።
በፌዴራል መንግስትና በሕወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ የሚያገኝ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም ድጋፍ በማድረግ የሰላም ሂደቱ ትልቅ ምሳሌ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያ ችግር በአፍሪካውያን መፈታቱ የፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ ዳግም የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አፍሪካውያን ለአፍሪካ ሰላም ልማት፣ እድገትና አንድነት በጋራ መስራት እንደሚችሉ የሳየ ክስተት ነውም ብለዋል።
ምሁራኑ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት ማገዝና መደገፍ እንዳለባቸው የጠቆሙት ዶክተር ሃይለየሱስ፤ በተለይም ስምምነቱን በሙያና በእውቅት የማገዝ አገራዊ ግዴታ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የነበረው የሰላም ውይይት ባለፈው ሳምንት በፕሪቶሪያ ከስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።