ቀጥታ፡

ሁለት የኢትዮጵያ የዕደ ጥበብ ምርቶች በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ምዝገባ የምስክር ወረቅት አገኙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 01 ቀን 2015 ሁለት የኢትዮጵያ የዕደ ጥበብ ምርቶች በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ምዝገባ የምስክር ወረቅት አገኙ።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሁለት የዕደ ጥበብ ምርቶችን በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በኩል በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ሆነው እንዲመዘገቡ ማድረጉን አስታውቋል።

በዚህም ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የንግድ ምልክት ምዝገባ የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡

የዕደ ጥበብ ምርቶችን በንግድ ምልክትነት (ብራንድ) ማስመዝገብ መቻሉ ኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነትን በማረጋገጥ ለማስጠበቅ እና ምርቶቹን ከፈጠራ መብት ስርቆት ለመታደግ እንደሚጠቅማት ተገልጿል።

የዕደ ጥበብ ውጤቶቹ በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) መመዝገባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ተሳታፊ ለመሆን እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡

በንግድ ምልክትነት የተመዘገቡት የዕደ ጥበብ ምርቶችም የሐረር ጌይ ሞኦት (አለላ ስፌት) እና የጋምቤላ ሉል ናቸው፡፡

የሐረር ጌይ ሞኦት (አለላ ስፌት) ምርት በሀረሪ ክልል በሰፊው የሚመረት ሲሆን በማህበረሰቡ ማንነት፣ እምነት፣ አኗኗር፣ ባህል፣ ልማድና ወግ ውስጥ የተለያዩ ፋይዳዎች ያሏቸው ሲሆኑ በምዝገባ ቁጥር LTM/8109/2015 መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

የጌይ ሞኦት 32 የሚደርሱ የስፌት ዓይነቶች እና ከ34 ዓይነት በላይ ዲዛይን ያላቸው ስነ ጥበባዊ ገፅታን የተላበሱ፣ ለስጦታ፣ ለመገልገያ እና ለትዕምርት ውክል የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

በሀረሪ ባህል ለሰርግ፣ ለሀዘን፣ ለስጦታ፣ ለቤት ማስጌጫነት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

የጋምቤላ ሉል ምርት በጋምቤላ ክልል በሰፊው የሚመረት ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውል እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ባህላዊ የዕደ ጥበብ ምርት ነው፡፡

ምርቱን ለማስተዋወቅ እና የበለጠ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኝ፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ግብዓት እንዲውል ለማድረግ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ተመላክቷል።

ምርቱን በዲዛይንና በስታንዳርድ በማሻሻል የምርቱን መለያ (ብራንድ) ምልክት በማዘጋጀት፣ በማልማት፣ በመጠበቅ ከምርቱ የሚገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ምልክት (ብራንድ) የምዝገባ የምስክር ወረቅት እንዲያገኝ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡

በዚህም ምርቱ በ LTM/8049/2015 ተመዝግቦ በዓለም አቀፍ ምድብ የንግድ ምልክት (ብራንድ) ምዝገባ የምስክር ወረቅት ማግኘቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም