ቀጥታ፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች የድርሻችንን እንወጣለን---የፖለቲካ ፓርቲዎች

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 30 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ መንግስት ለሚያካሄደው የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።


በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ - ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋድቤል ቦል፤ የፌዴራል መንግስትና ህወሓት ያደረጉት የሰላም ስምምነት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ እንደሚደግፉት ገልጸዋል።
መንግስት ለሚካሄዳቸው የሰላም ሂደትና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ስራዎችን በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የኢፌዴሪ መንግስት ከህወሓት ጋር የደረሰበት የሰላም ስምምነት የጦርነቱ ፍፃሜ እንዲሆን ሲጠብቁት የነበረ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ /ጋህነን/ አመራር አቶ ተዘራ ኃይለማሪያም ናቸው።
ስምምነቱ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን በማስፋን የእድገትና የብልጽግና ጉዞ ለማፋጣን የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ የሰላም ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ሁላችንም ከመንግስት ጋር ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ /ጋህፍሰልዴን/ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቾል ኮዎር በበኩላቸው፤ ሰላም ለዜጎች ድህንነት፣ ለሀገር እድገትና ልማት ዓይነተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ይህንን ለማሳካት የተደረገው ስምምነት ከልብ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ፓርቲያቸው አቅም በፈቀደ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም አቶ ቾል ገልጸዋል።
በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተካሄደው የሰላም ንግግር ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም፤ በአንድ ሀገር ከአንድ መከላከያ በላይ አያስፈልግም የሚሉት በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ማግኘቱ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ድል መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ሕጋዊነትን ማስፈን ለአንድ ሀገር ህልውና መሰረት በመሆኑ በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕገ ወጥ ምርጫ ተሰርዞ በህጋዊ ምርጫ እንዲተካ የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ለሰላም ስምምነቱ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ መጠየቃቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም