ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ የግሉ ሴክተርን ባሳተፈ መልኩ የወጣቶችን የስራ ዕድል ፈጠራ ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 የኢኖቬሸንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የግሉን ሴክተር በመስኩ በስፋት በማሳተፍ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የ2015 የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሚኒስቴሩ በዘርፉ እያደገ ያለውን የስራ ዕድል ፈጠራ በማጎልበት የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ በስፋት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።

በተጨማሪ ሚኒስቴሩ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ዕድል ፈጠራን ማጎልበት እና የፈጠራ አቅምን መገንባት ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ኢትዮጵያን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

በቡራዩ የተገነባው የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት መጠናቀኑን አድንቀው፤ የትምህርት ቤቱ ቀሪ ግብዓቶችና ህጋዊ ማዕቀፎች ተሟልተው ወጣቶች በፍጥነት ወደ ስልጠና መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ስራዎቹን ማስተዋወቅ፣ ተደራሽ የማደረግና የለሙ ቴክኖሎጂዎችን ከማሸጋገር አንጻርም ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በአሌክትሮኒክስ ግብይት ረገድ መደበኛ ባልሆኑ ፕላትፎርሞች የሚደረጉ ግብይቶችንም ወደ ሕጋዊ ስርዓት እንዲገቡ ማድረግና የመንግስትን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም እንዲሁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው ሚኒስትሩ እንደአዲስ በተዋቀረ በአጭር ጊዜ ራሱን አደራጅቶ በርካታ የለውጥ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መስክ ከተቋማት ጋር በመቀናጀት የህዝቡን የቴክኖሎጂ አገልግሎት ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች ስለመከናወናቸው ገልጸዋል።

ለአብነትም 20 የፌዴራል ተቋማት በሙያና ቴክኒክ በመደገፍ አገልግሎታቸውን በኦንላይን ስርዓት እንዲዘረጉ በማድረግ ግብይትና አገልግሎታቸውን ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ክፍተቶችንም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት በመስራት እንደሚያሻሽለ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም