በጅቡቲ ወደብ ከመርከብ ላይ በቀጥታ መጫን የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅቡቲ ወደብ ከመርከብ ላይ በቀጥታ መጫን የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) ከጅቡቲ የወደብ አገልግሎት ጋር በመሆን ቀደም ሲል በጭነት ማራገፍና ማጓጓዝ ረገድ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አሰራሮችን ሊተገብሩ ነው።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የጅቡቲ ወደብ ተናበው በመስራታቸው በመርከብ ጭነት አገልግሎት እና በሎጀስቲክስ ዘርፍ ውጤታማ ስራ መስራት አስችሏል ሲሉ የዶራህሌ መልቲፐርፐዝ የስራ ኃላፊ ገለፁ፡፡
የዶራህሌ መልቲፐርፐዝ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ኦፊሰር ኢድሪስ ዶሆር አህመድ የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የጅቡቲ ወደብ ግንኙነት ከጀመረበት ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የጅቡቲ ወደብ ተናበው መስራታቸው በመርከብ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ውጤታማ ስራ እንዲከናወን አድርጓል ሲሉም ኃላፊው አስታውቀዋል።
ስራው በየሰዓታቱ እንድንገናኝ የሚያስገድድ እንደመሆኑ መጠን የመርከቦችን መድረሻ፣ የመርከብ ላይ ጭነት ማራገፍ፣ የየብስ ከባድ ተሽከርካሪ ጭነቶችን እና የባቡር ጭነቶችን አንድ ላይ አቅደን መስራታችን ክንውናችንን ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ከመርከብ ላይ በቀጥታ መጫን የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ዕውን እንደሚያደርጉ አስረድተው የ2015 የአፈር ማዳበሪያ ቀደም ሲል ሲወስደው ከነበረው ባጠረ ጊዜ ወደ ሚፈለግበት ስፍራ ማድረስ የሚያስችል አሰራሮችን መዘርጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የጅቡቲ ወደብ በየጊዜው በሚያጋጥሙ ማነቆዎች ላይ የመነጋገርና የመፍታት ባህል እንዳላቸውም አብራርተዋል።
ከዓመታት በፊት በጅቡቲ ወደብ ላይ የመርከቦች መቆሚያ መጨናነቅ፣ ጭነቶችን በወቅቱ ያለማራገፍና ያለማንሳት እና መሰል ችግሮች ነበሩብን ያሉት ሀላፊው እነዚህን ችግሮች መፍታት መቻሉን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ብቃት ባላቸው አመራሮቹ አማካይነት የስራ ቅልጥፍና በማምጣት እና ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ውጤታማ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል፡፡
በቅርብ ዓመታት የመርከቦችን መድረሻ ቀናትን በዕቅድ በመምራት የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ ተችሏል ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በመዘጋጀቱ ለኢትዮጵያ መንግስት፣ ለግብርና ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ሃላፊው ክብሩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን ነው ብለዋል።
በተለይ ለጅቡቲ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደመሆኑ ይህን ስራ በልዩ ትኩረት የምንሰራው ነው ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡