ቀጥታ፡

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶች ጨምሮ ከ28 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ሥራ እየተካሄደ ነው-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶች ጨምሮ ከ28 ሺህ 550 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶችና ድልድዮች በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ የመጠገን ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ የመንገድ ፈንድ ዳይሬክተር ኢንጅነር ካሳሁን በጂጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አስተዳድሩ በበጀት ዓመቱ በአገሪቱ ከ28 ሺህ 550 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መሰረተ ልማት ለመጠገን አቅዶ እየሰራ ነው።

የመንገዶች ጥገና የሚከናወነውም ከመንግስት በጀት እና ከተለያዩ ገቢዎች በተሰበሰበ ከ5 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በሩብ አመቱ ለመንገድ ጥገና ስራዎች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፤ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው መንገዶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ ነው ያሉት።

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መንገድ ጥገና በመደረጉም፤ ክፉኛ የተጎዱ መንገዶች አሁን ላይ ወደነበሩበት ተመልሰው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም እስካሁን በአፋር ክልል 280፣ በአማራ ክልል ደግሞ 274 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና መከናወኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም