ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30/2015 ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር አስታወቀ።
ሕዳር 6 እና 7 ቀን 2015 ዓ.ም "ዓለም አቀፋዊ አጋርነትን ማዳበር" በሚል ቃል በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጉባኤ ማህበሩ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በትብብር ያዘጋጀው ነው።
ጉባኤው፤ በኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሲሣይ አስማረ የንግድ ጉባዔውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ጉባኤው የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አምራች እና ላኪዎች ዓለም አቀፍ ልምዶችን እንዲቀስሙ ያስችላል።
በጉባኤው ከ150 በላይ የአገር ውስጥ ላኪዎች፣ የእርሻ ግብዓት እና ማሽነሪ አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።
ከ12 የውጭ አገራት ደግሞ ከ100 በላይ የዘርፉ ተዋንያን የሚታደሙ ሲሆን የጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ፓኪስታን፣ ቱርክ፣ እስራኤል፣ ኔዘርላንድ፣ ህንድና እንግሊዝ ተሳታፊ አገራት ናቸው።
በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ዘርፍ ነባራዊ ሁኔታን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች በመድረኩ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም አቶ ሲሣይ ገልጸዋል።
ጉባኤው የአገር ውስጥ ገዥዎች፣ ላኪዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ከውጭ አቻዎቻቸው የነበራቸውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ አዳዲስ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የሽያጭ ውሎችን ለመፈራረም ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።