ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት በየደረጃው ባሉ አደረጃጀቶች ድጋፍ ይደረጋል- በብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት በየደረጃው ባሉ አደረጃጀቶች ድጋፍ ይደረጋል- በብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ
እንጅባራ (ኢዜአ) ጥቅምት 30/2015 በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው ባሉ አደረጃጀቶች ድጋፍ እንደሚደረግ በብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዛህራ ሑሙድ አስታወቁ።
"የጎህ ቃል ኪዳንን ፈፅመን ከፍታው ላይ እንገኛለን" በሚል መሪ ሀሳብ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የ2015 የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤና የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዛህራ ሑሙድ በወቅቱ እንዳሉት በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ፊታችንን በሙሉ አቅም ወደ ልማት እንድናዞር ያስችለናል ።
በጦርነት ወቅት ሴቶች ዋንኛ ተጎጂዎች መሆናቸውን አስታውሰው የሠላም አየር መተንፈስ የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሱ በልማቱ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ለማስቀጠል መደላድል የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
ሴቶች ሀገር ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት ለሰላም መስፈን አይነተኛ ሚና ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውሰው የሊጉ አባላትም በሀገራዊ ልማትና ሰላም ሥራዎች ላይ በንቃት ሲሳተፉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ከተደረሰው የሰላም ስምምነት ትሩፋት ሴቶች ዋንኛ ተጠቃሚ መሆቸውን ያመለከቱት ወይዘሮ ዛህራ ለስምምነቱ ስኬታማነት በየደራጃው ባሉ አደረጃጀቶች ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው "አሁን ላይ ኢትዮጵያ ባቀደችው መሠረት ወደ ስኬት እንድታመራ ሴቶች በአደረጃጀቶቻቸው እያገዙ ይገኛሉ" ብለዋል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለውጤት እንዲበቃም የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አመላክተዋል።
"የሰላም ስምምነቱ የሀገር ሉአላዊነትን የሚያጸናና ጣልቃ ገብነትን የሚቀንስ ነው" ያሉት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ ዞን ሴቶች ሊግ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ የሻሽወርቅ መላኩ ናቸው።
"በዞኑ ባለን የሊጉ መዋቅር በመጠቀም በስምምነቱ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ በትክክል ወደ ህዝቡ እንዲወርድ በማድረግ ለዘላቂ ሰላማችን መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ በበኩላቸው ሴቶች የሀገርን ሰላም የማስጠበቅ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል ።
አሁን ላይ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እውን በማድረግ ሂደትም ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል ።
የሰላም ስምምነቱን ፋይዳ በተገቢው በመገንዘብና በማስገንዘብ በዘላቂነት እንዲፈፀም ፓርቲው ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል ።
መድረኩ ላይ ከፌደራል፣ ክልልና ዞን የመጡ አመራሮችና የሊጉ አባላት ተሳትፈዋል።