በጣና ሐይቅ ብዝሐ-ሕይወትን በጠበቀ መልኩ በተጀመረው የአሳ እርባታ ስራ ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በጣና ሐይቅ ብዝሐ-ሕይወትን በጠበቀ መልኩ በተጀመረው የአሳ እርባታ ስራ ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30/2015 በጣና ሐይቅ ብዝሐ-ሕይወትን በጠበቀ መልኩ በተጀመረው የአሳ እርባታ ስራ ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች
የጣና ሐይቅ 21 የአሳ አይነቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ በውስጡ 28 የዓሳ ዝርያዎችን ያቀፈና ለአሣ እርባታ ዕምቅ አቅም ያለው የውሃ ሀብት ነው።
ነገር ግን ከ21 ወረዳዎች እና 347 ቀበሌዎች ያላነሱ አካባቢያዎችን ያቀፈው የጣና ሐይቅ ተፋሰስ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ብዝሀ ሕይወቱ እየተጎዳ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
ከሕገ ወጥ የአሳ ማስገር እንቅስቃሴዎች ጋር ተዳምሮ የጣና ሐይቅ አሳ ሀብቱ መመናመን አሁን ላይ 'አሳ አበላሻለሁ ጣና ዳር ነው ቤቴ' እንደሚለው ዘፈን አሣ እንደልብ ማግኘት በተጠቃሚው ዘንድ ተናፍቋል።
አሣ በስፋት ከሚሰገርባቸው አካባቢዎች አንዱ በጣና ሐይቅ በስተደቡብ ምዕራብ በሰሜን አቸፈር ወረዳ የምትገኘው ቁንዝላ ከተማ ነበረች።
ከከተማዋ ወጣቶች መካከል ገነት ፍትሐነገሥት እና መንግስቱ ምስጋናው፤ ሕገወጥ አሳ ማስገር በአካባቢው አሳ ሀብት ላይ አደጋ ደቅኗል ይላሉ።
ወጣቶቹ አሁን ላይ በቁንዝላ የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ተደራጅተው፤ የሐይቁን ብዝሃ ሕይወት ጠብቀው፤ በዘመናዊ አሣ እርባታ አሳን ለማቅረብ ወደስራ ገብተዋል።
በሐይቁ ላይ የሚንሳፈፉ 'ኬጂ' የሚሰኙ ድንኳን መሰል የእርባታ ገንዳዎችን በመጠቀም፤ ከወራት በፊት የጀመሩት የእርባታ ሂደትም አሁን ላይ ተሰፋ ሰጭ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
ከወራት በኋላ በመጀመሪያው ዙር የተሻለ የአሳ ምርት ለማግኘት ብሩህ ተስፋ እንደሰነቁ የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ ሌሎች ወጣቶች በቀጣይ ውጤታማነታቸውን አይተው ፈለጋቸውን ለመከተል መነሳሳት እንደፈጠሩም ያነሳሉ።
በቁንዝላ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት የእንስሳት ሃብት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተሾመ ደርሶ፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ ወጣቶችን አሣን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።
በተጨማሪም በጣና ኃይቅ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እየተስተዋለ ያለውን የአሳ ምርት እጥረት መቅረፍና ብዝሀ ሕይወቱን ጠብቆ አሳ በዘላቂነት እንዲመረት ማስተዋወቅ መሆኑን እንዲሁ።
በዚህም ከስድስት ወራት በፊት 10 ወጣቶችን በማደራጀት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጣና ሐይቅ ላይ የተጀመረው በ'ኬጂ' አሳን የማርባት ቴክኖሎጂ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለአሳ ምርት አቅርቦት ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ቴክኖሎጂው በባህርዳር አሳ ምርምር ማዕከል የወጡ የተሻሻሉ የአሣ ጫጩቶችን በባህር ወስጥ በሚገኙ እንስሳትም ሆነ በአዋዕፍት ጥቃት በማይጋለጡበት አግባብ የሚራቡበት መንገድ ነው።
እስካሁን በ10 ኬጂዎች ላይ 48 ሺህ ጫጩቶች የገቡ ሲሆን በቀጣይም በአጠቃላይ 20 የማርቢያ ኬጂዎችን በማዘጋጀት 120 ሺህ የአሣ ጫጩቶች እንደሚገቡ ገልጸዋል።
ከሰባት ወራት በኋላ ጫጩቶች ለገበያ እንደሚደርሱ ገልጸው፤ በዓመት በአንድ ማራቢያ ኬጂ 300 ሺህ ብር እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ከ15 ሚሊየን ዩሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የቁንዝላ የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት ለከተማዋ ትንሳኤ እየሆነ መምጣቱን ወጣቶቹ ገልጸዋል።
የቁንዝላ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እጅጉ አየለ፤ ድንቅ መልክዓ ምድር የተቸረችው እና የጣና ሐይቅ ዳር ታሪካዊ ስፍራዎችን ያቀፈችው የቁንዝላ ከተማ አሁን ላይ በከፍተኛ መነቃቃት ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች መምጣታቸው እና ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈው የዱርቤቱ- መተማ አስፓልት መንገድ ፕሮጀክት መጀመሩ በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም መስክ በርካታ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ እንዲያቀርቡ እድል መፍጠሩን አረጋግጠዋል።
ቁንዝላ ከተማ 4 ሺህ 50 ሄክታር መሬትን ያካለለ የተቀናጀ ማስተር ፕላንም በኔዘርላንድ ኤምባሲ ድጋፍ እንደተዘጋጀላት ገልጸዋል።
'ቁንዝላ እንደ ጎርጎራ በአገር አቀፍ ደረጃ እንድትለማ የምንጠብቃት ከተማ ናት' ያሉት አቶ እጅጉ፤ በሁሉም ኢኮኖሚ ዘርፎች መሰማራት ለሚሹ ባለሀብቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ነው የገለጹት።
በተመሳሳይ ወጣት ገነተ ፍትሃነገስት በከተማዋ ላይ እየታየ ያለው መነቃቃት ለነዋሪዎቹ ተስፋን የሰነቀ መሆኑን ይናገራል፡፡