ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነባው የዓሊ-ዋቤ ድልድይና አስፋልት መንገድ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነባው የዓሊ-ዋቤ ድልድይና አስፋልት መንገድ ተጠናቀቀ
አዲስ አባባ / ኢዜአ/ ጥቅምት 30/2015 ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነባው የዓሊ ከተማ-ዋቤ ድልድይና ኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በፌደራል መንግስት የተገነባውና ሁለት ቢሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ሦስት ሚሊዮን ስልሳ ሺህ ስድስት መቶ ሰባ አንድ ብር ወጪ የተደረገበት ይህ መንገድ 56.5 ኪ.ሜ ርዝመተ አለው ።
የባሌ ሮቤ አካባቢ ግንባታ ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ከድር ረዲ(ኢንጅነር) ፕሮጀክቱ የአራት ድልድዮች ግንባታና ከባድ የቆረጣ ሥራን በማለፍ በታለመት ጊዜ ተጠናቅቋል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ዕውን መሆን በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን የስንዴ፣ ገብስ እና የፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶችን በስፋት እና በጥራት ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማድረስ ኢኮኖሚያዊ ፍይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም መንገዱ በዋናነት ሮቤ፣ ዓሊ እና ዋቤ ከተሞችን በቅርበት በማገናኘት፥ የቱሪዝም መዳረሻ የሆኑትን የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የሳነቴ አምባ እና የዲንሾ ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ኢንጅነር ከድር ገልጸዋል።
በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው አበበ በበኩላቸው፥ ከዚህ ቀደም የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ለተለያዩ እንግልቶች ይዳረግ እንደነበር አስታውሰዋል።
የመንገዱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው መንገዱ በማለቁ ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንደታደጋቸው ተናግረዋል ሲል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል ።