ቀጥታ፡

የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ነው-ማህበሩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 “በመንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፍሪካውያን በጋራ ከቆሙ ችግራቸውን በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ነው” ሲል የተባበሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ አስታወቀ።

ማህበሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

“የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን ይፈታል” በሚል እሳቤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ መፍታት እንደምትችል በተደጋጋሚ ጊዜ ሲሞግት መቆየቱንም አስታውሷል።

በሕብረቱ መሪነት የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት መስማማታቸው ማህበሩን እንዳስደሰተውና ስምምነቱ “አፍሪካውያን በጋራና በቅንነት ከሰሩ ሁሉን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያስመሰከረ ነው” ብሏል።

የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን መልካም ምኞቱን የገለጸ ሲሆን ለስምምነቱ ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።

የጋራ ታሪክና የባህል እሴቶች ያላቸው ዜጎች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በጽናት ትሻገራለች ነው ያለው ማህበሩ በመግለጫው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም