የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የፊፋን መመዘኛዎች መሰረት ያደረገው ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራዎች ሊሰሩለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የፊፋን መመዘኛዎች መሰረት ያደረገው ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራዎች ሊሰሩለት ነው
ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራዎች እንደሚሰሩለት ተገለጸ።
የስታዲየሙ 2ኛ ዙር ስራዎች ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው።
ለስታዲየሙ ማጠናቀቂያ የአማራ ክልል 700 ሚሊዮን ብር ቀሪውን 300 ሚሊየን ብር ደግሞ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እንደሚሸፈን ተገልጿል።
በሁለተኛው ዙር የስታድዮሙ ማጠናቀቂያ ግንባታ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የሜዳ ጥራት ማሻሻያ፣ የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ መቀመጫ ወንበር መግጠም፣ መሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎችም እንደሚገኙበት ታውቋል።
የማጠናቀቂያ ስራው ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ወደ ማስተናጋድ እንዲመለስ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
የሁለተኛው ዙር ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መመዘኛ መስፈርቶችን ባለማሟላቱ ምክንያት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ ማገዱ ይታወሳል።
በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላለፈው አንድ ዓመት ጨዋታውን ከሀገር ውጪ እንዲያደርግ አስገድዶታል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።