ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ልማት 10 ሺህ ሄክታር መሬት በሽንኩርትና ቲማቲም ዘርተሸፍኗል

አምቦ (ኢዜአ) ጥቅምት 30/2015 በምዕራብ ሸዋ ዞን በአንደኛ ዙር የበጋ መስኖ ልማት እስካሁን 10 ሺህ ሄክታር መሬት  በሽንኩርትና ቲማቲም ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ ልማት ባለሙያ ገዛኸኝ ዲንሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በሁለት ዙር 56 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ በተለያዩ ስብሎች ይሸፈናል ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም በአንደኛ ዙር ለማልማት ከታቀደው 31 ሺህ ሄክታር መሬት 10 ሺህ ሄክታሩ ታርሶ በቀይ ሽንኩርትና ቲማቲም ተሸፍኗል ነው ያሉት።

በዞኑ አትክትልና ፍሬፍሬ እንዲሁም በቆሎ በመስኖ ልማት በስፋት እንደሚሰራበት አንስተው 150 የሚሆኑ የውሃ መሣቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሩ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለምርት ማሳደጊያ የሚውል 30 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚሰራጭ እና በአርሶ አደሩ የተዘጋጀ 200 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያም ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

በተጨማሪም ከ320 ሺህ ኩንታል በላይ የድንችና የበቆሎ እንዲሁም ከ250 ሺህ ኪሎግራም በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር አቅርቦት እንደሚኖር አመላክተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በመስኖ ልማቱ ከ62 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ይሆናል።

የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር በሬቻ በቀለ ባለፈው ዓመት በመስኖ ካለሙት የጓሮ አትክልት ሽያጭ 200 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

"በዚህ ዓመትም በመጀመሪያው ዙር መስኖ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ ማልማት ጀምሬያለሁ" ብለዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ 54 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም