በግሪን ሀውስ ቴክኖሎጂ አትክልት በማልማት ኑሯቸውን መለወጥ መቻላቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 በግሪን ሀውስ ቴክኖሎጂ የጓሮ ማሳቸው ላይ አትክልት በማልማት ኑሯቸውን መለውጥ መቻላቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

ግሪን ሀውስ በፕላስቲክ በተሸፈነ አነስተኛ ማሳ ውስጥ ከዝናብ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ውሃ በማጠጣት አትክልት የማልማት ቴክኖሎጂ ነው።

በኔዘርላንድ መንግስት ድጋፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ራስ ገዝ ሆኖ በሚንቀሳቀሰው የውሃ እና መሬት ሀብት ማዕከል በሚተገበረው የቁንዝላ የተቀናጀ ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ አንዱ ግብ ነው።

በዚህም ፕሮጀክቱ ግሪን ሀውስ የተሰኘውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አርሶ አደሮች በጓሯቸው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ በ2014/15 ምርት ዘመን ለሰባት አርሶ አደሮች የግሪን ሀውሶችን ገንብቷል።

በምዕራብ ጎጃም ሰሜን አቸፈር ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ከፋለ ሁነኛው መጀመሪያ አካባቢ በግሪን ሀውስ ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬ እንደነበራቸው ገልጸው ተክኖሎጂውን ተጠቅመው ማምረት ከጀመሩ በኋላ ግን የተሻለ ምርት እንዲሚያስገኝ ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ፡፡

140 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው የጓሮ ማሳ ላይ በግሪን ሀውስ ቴክኖሎጂ ቲማቲም በማልማት ከ20 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም ይናገራሉ።

ባለቤታቸው ወይዘሮ ይህዓለም አበበም በፕሮጀክቱ ድጋፍ ጓሯቸውን በማልማት የቤተሰባቸውን ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ይናገራሉ።

በተመሳሳይ የሳንክራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በታ አስማረ በግሪን ሀውስ ውስጥ ባለሙት ቲማቲም ውጤታማ በመሆናቸው ልጆቻቸውን በአግባቡ እንዲያስተምሩ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በተለይም የዝናብ ውሃን በማጠራቀም ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱ እየተጠቀሙበት መሆኑን በማንሳት።

በቁንዝላ የተቀናጀ ፕሮጀክቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ግዛቸው አባተ የግሪን ሀውስ ቴክኖሎጂ የቲማቲም ምርታማነትን ለመጨመርና በሽታን ለመከላከል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ግሪን ሀውስ የአትክልት ሰብሎችን እያፈራረቁ በዓመት ሶስት ጊዜ ማልማት የሚያስችል ለሰብል ቁጥጥር ምቹ የሆነ አሰራር መሆኑን ነው ያነሱት።

ፕሮጀክቱ እንደሙከራ በሰባት አርሶ አደሮች ጓሮ ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ መጀመሩን አስታውሰው የአካባቢው አርሶ አደሮች ውጤታማነቱን በማየት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በዘንድሮው ዓመት ብቻ 21 ተጨማሪ ግሪን ሀውሶች እንደሚገነቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም