ቀጥታ፡

አሊ ቢራ በጥበብ ደምቆ በሕይወት ዘመኑ የሚጠበቅበትን ለትውልዱ አበርክቶ ያለፈ ድንቅ አርቲስት ነው - የሙያ ባልደረቦቹ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 29/2015 አሊ ቢራ በጥበብ ደምቆ፣ በህይወት ዘመኑ የሚጠበቅበትን ለትውልዱ አበርክቶ ያለፈ ድንቅ ድምጻዊ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርቲስቱ የሙያ ባልደረቦች ገለጹ፡፡

ለአርቲስት አሊ ቢራ አስክሬን ሽኝት መርሃ ግብር  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሙያ ባልደረቦቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል፡፡

በሽኝት መርሐግብሩ ላይ ለኢዜአ አስተያታቸውን የሰጡት የሙያ ባልደረቦቹ አሊ ቢራ በስራዎቹ ሕዝብን ያስተሳሰረ፣ ሀገሩን የሚወድ፣ ደግና ሩህሩህ እንደነበር ተናግረዋል፡፡  

የአርቲስት አሊ ቢራ የቅርብ ወዳጅ የሆነው መሃመድ ቆጴ አርቲስት አሊ ቢራ ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት በሙያው የታገለ የጥበብ ሰው መሆኑን ይናገራል፡፡

አርቲስቱ በስድስት ቋንቋ በመጫወት በሙዚቃ ጥላ ስር ህዝብን ያሰባሰበ ነው ያለው መሃመድ ቆጴ  የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ  ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የራሱን መሰረት መጣሉንም አንስቷል፡፡

አሊ ቢራ በጥበብ ደምቆ ያማረ፣ ህዝብን አስተምሮ ያዝናና እንዲሁም ህዝብ ላይ የነበረ ጭቆናና ግፍ እንዲወገድ የታገለ የነጻነት ሰው መሆኑን በመግለጽ፡፡

ታዋቂው አርቲስት ጸጋዬ ደንደና /ሰዮ/ " ጥበብ አንድ ትልቅ ሰው አጥታለች " አሊ ቢራ ትውልዱ በትምህርት እንዲጎለብት የራሱን አሻራ ያኖረ እና በስልጣኔ መንገድ እንዲጓዝ ያደረግ ድንቅ የህዝብ ልጅ ነው በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ታዋቂው ሙዚቀኛ ሻምበል በላይነህ  በበኩሉ አሊ ቢራ አገሩን የሚወድ፣ ለሁሉም ዜጎች ትልቅ ክብር ያለው አርቲስት  ነው ብሏል፡፡

ለበርካታ ዓመታት አብረው መስራታቸውንም ገልጾ ከአሊ ቢራም በርካታ ሙያዊ እውቀቶችን ማግኘቱን ጠቁሟል፡፡

የሙያ አጋሮቹ የአሁኑ ትውልድ ከአርቲስት አሊ ቢራ ስራዎች በመማር የተሻለ ስራ ለመስራት ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ በአዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ75 ዓመቱ ከትናንት በስቲያ ሕይወቱ ማለፉ ይታወቃል።

አርቲስት አሊ ቢራ በህይወት ዘመኑ ከ267 በላይ ሙዚቃዎች ያበረከተ ሲሆን፤የመጀመሪያ አልበሙን  በ1971 ዓ.ም ለህዝብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም