ቀጥታ፡

በብየዳ ሙያ ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል - የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ( ኢዜአ) ጥቅምት 29/2015 በብየዳ የሙያ ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የብየዳ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ማዕከል በዘርፉ ላሰለጠናቸው ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሰጥቷል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤  ማዕከሉ ከደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የብየዳ ኢንስቲትዩት እውቅና ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ይህም ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

ለኢንዱስትሪ እድገት የብየዳ ባለሙያዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው መንግስት ባለፉት ዓመታት  የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ተደራሽነት የሚያሰፉ ስራዎችን ማከናወኑን  ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም አገሪቱ ለምታከናውነው የልማት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ፣ በብየዳ ዘርፍ ላይ የሚስተዋለውን የባለሙያ ክፍተት ለመሙላትና  ሰልጣኞች ጥራት ያለው እውቀት እንዲጨብጡ ሰፊ ስራ እናከናውናለን ነው ያሉት፡፡

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት  ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እንየው ጌትነት እንዳሉት ለማዕከሉ የተሰጠው እውቅና በብየዳ ዘርፍ ላይ በርካታ የሰው ሀይል ለማፍራት እና ወደ ስራ ለማስገባት በር ይከፍታል፡፡

ለብየዳ ዘርፉ እውቅና መሰጠቱ በትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ፤ፋብሪካዎች እና ሌሎች ስራዎች ላይ በብየዳ ሙያ ላይ የተሰማራ ሙያተኛን ከውጭ አገር ከማስመጣት ይልቅ በአገር ውስጥ ሙያተኞችን እንድንጠቀም ያስችላል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም