በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በቱሪዝምና ሆቴል የስራ ዘርፍ ተሰማርተዋል - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በቱሪዝምና ሆቴል የስራ ዘርፍ ተሰማርተዋል - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት
አዲስ አበባ (ኢዜአ ) ጥቅምት 29 ቀን 2015 "በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ ነው" ሲል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።
የቱሪዝም ዘርፉ ለ10 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ገልጿል።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለስራ እድል ፈጠራና ለአገር የሚያስገኘውን ገቢ መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ዛሬ አካሄዷል።
የኢኒስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም "በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለ10 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለ በጥናት ተረጋግጧል" ሲሉ ይገልጻሉ።
ሆቴልና ቱሪዝም በሚፈለገው ልክ እድገት ባለማስመዝገቡም በአሁን ወቅት ከሁለት ሚሊዮን ያልበለጠ ዜጋ ብቻ በዘርፉ መሰማራቱን ተናግረዋል።
ከቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩቱ በርካታ ወጣቶች የሙያ ስልጠና በመውሰድ እየወጡ ቢሆንም የስራ እድል እያገኙ አይደለም ብለዋል።
ኢኒስቲትዩቱ ችግሩን ለመፍታት ፕሮጀክት ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማትም በትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም ብቃትና ክህሎት ያለው ባለሙያ በማፍራት ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚሆን የሰው ኃይል ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ከተለያዩ የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ቢኖሩም የክህሎት ክፍተት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ተቋሙ በትብብር ለመስራት ያቀረበው ጥሪ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችል ጥራትና ብቃት ያለው የሰው ሃይል እንዲኖር ለማድረግ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።