በኢትዮጵያ የተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶች አፍሪካውያን የመሰረተ ልማት ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ናቸው-ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶች አፍሪካውያን የመሰረተ ልማት ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ናቸው-ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 29/2015 በኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶች አፍሪካዊያን የመሰረተ ልማት ችግሮቻቸውን በራስ አቅም መፍታት እንደሚችሉ ማሳያዎች መሆናቸውን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየው 8ኛው የአፍሪካ ማሃንዲሶች ሳምንት እና 6ኛው ኢንጂነሪንግ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አፍሪካዊያን እርስ በርስ የሚያስተሳስራቸው የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ይህም አፍሪካ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የኢኮኖሚ አድገቷን እንዳታፋጥን ማነቆ መሆኑን አንስተው አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና አፍሪካዊያንን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካውያንን መፃኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠትና ከሚፈለገው በታች የሆነውን የእርስ በርስ ትብብር ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለውጭ የዲዛይን ባለሙያዎችና ግንባታ ሰራተኞች ይሰጡ የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲከናወኑ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለአብነት በአዲስ አበባ ዙሪያ የተሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ባለሙያዎች፣ የግንባታ ተቋራጮችና ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸው ይህም አፍሪካዊያን የሚገጥማቸውን የመሰረተ ልማት ችግር በራሳቸው ባለሙያዎች መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
የኢንጂነሪንግ ትምህርት መጠናከር እና የአቅም ግንባታ ስራዎች ለመሰረተ ልማት መስፋፋት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ፤ ከዚህ አኳያ አፍሪካውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ አለብን ብለዋል፡፡
አህጉራዊ ባለሙያዎች ለአፍሪካዊያንን ኑሮ መሻሻል ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ በአግባቡ ስራ ላይ ማሳተፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡