የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል-የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል-የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 29/2015 የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት፣ በርካታ ወንዞችና፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ያላት አገር ብትሆንም የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ሳትችል ዘመናትን ተሻግራለች፡፡
የግብርና ስርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመደገፍና ለመስኖ ልማት የሚፈለገውን ያህል ትኩረት አለመስጠት ደግሞ ዘርፍ ውጤታማ አለመሆን በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህ አኳያ መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያ አሁን ላይ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል ባለፈ ለወጭ ንግድ ማቅረብ በምትችልበት የሽግግር ሂደት ላይ ትገኛለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የስንዴ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትጀምራለች፡፡
ከስንዴ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አማካኝነት በዶሮ፣ ማርና ወተት ላይ እየሰራች ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጡ ሰራ ደግሞ ከመንግስት ባሻገር የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ እሙን ነው፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ እንደሚሉት፤ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ከመቻል ባሻገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት በበጎ እንደማይመለከቱት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ በጋራ መቆም እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም በመስኩ አበረታች ስራ እየተከናወነ መሆኑን መገንዘብ ችለናል ነው ያሉት፡፡
"የፖለቲካ ልዩነት አገርን በጋራ ከማልማት የሚከለክል አይደለም" ያሉት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ልማት ላይ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ደግሞ ምክር ቤቱ የበኩሉን ሚና ይወጣል ነው ያሉት፡፡
በዘንድሮ በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡