ምክር ቤቱ የሁለት ተቋማትን የቦርድ አመራሮች ሹመት መርምሮ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የሁለት ተቋማትን የቦርድ አመራሮች ሹመት መርምሮ አጸደቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 29/ 2015 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የቦርድ ሰብሳቢና አባላትን ሹመት መርምሮ አጸደቀ፡፡
የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የሁለቱንም ተቋማት እጩ የቦርድ ሰብሳቢና አባላትን ምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፤የእጩዎቹ የአመራርነት የምልመላ ሂደት እውቀትና ዝንባሌን፣ አሳታፊነትን፣ እንዲሁም ፍላጎትና ዝግጁነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ለሁለቱ ተቋማት የቀረቡ እጩ የቦርድ አባላትን ግለ-ታሪክ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ሚኒስትሩ፤ በትምህርት ዝግጅታቸው እና ባካበቱት የስራ ልምድ ተቋማቱን የመምራት እንዲሁም ሀገርና ሕዝብን በብቃትና በቁርጠኝነት ለማገልገል አቅም ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ለሁለቱም ተቋማት ለቦርድ ሰብሳቢነት እና አባልነት የቀረቡ እጩዎች ኢትዮጵያዊነትን የተላበሱ፣ ሀገርና ሕዝብን በብቃትና በትጋት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ሹመቶች ወደ ምክር ቤቱ ሲመጡ በደንብ ተመርምረው ሊጸድቁ እንደሚገባ፤ ከአዋጁ ጋር የማይጣረሱ መሆን እንዳለባቸው እና የሴቶችን ተሳትፎ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት የምክር ቤት አባላት ጠቁመዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ከምክር ቤቱ ለተነሱ አስተያየቶች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ የሴቶች ተሳትፎ ላይ ከቁጥር አንጻር የተነሳው ትክክል እንደሆነ እና እንደ ግብዓት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸው በአንጻሩ በእጩነት የቀረቡት የቦርድ አመራሮች ሹመት ከአዋጁ ጋር የማይጣረስ እንደሆነ ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በእጩነት የቀረቡትን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢና አባላት ሹመት ውሳኔ ቁጥር 2/2015 በማድረግ በሶስት ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል፡፡
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬት የቦርድ አባል ሆነው የተሾሙ፡-
- ዶክተር ለገሰ ቱሉ……ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት…. ሰባሳቢ
- አብዱልዋሳ አብዱላህ…….ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል…አባል
- አቶ ታረቀኝ ቡልቡልታ…..ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር…….አባል
- አቶ ጃፋር በድሩ……ከውጭ ግንኙነት ኢኒስቲትውት….አባል
- አቶ መሳፍንት ተፈራ…..ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት…አባል
- ዶክተር ንጉሴ ተፈራ…..የሚዲያ ባለሞያ…አባል
- አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም…….አዲስ አበባ የመንግስት ንብረት አስተዳደር …አባል
- ወይዘሮ አመለወርቅ ህዝቄል.. ከትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ባለሞያ..አባል
- ረዳት ፕሮፌሰር ሙና አቡባከር….አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር…አባል
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢነትና አባልነት በእጩነት የቀረበለትን ሹመት ውሳኔ ቁጥር 3/2015 በማድረግ በአንድ ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል ሲል ምክርቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላት ሆነው የተሾሙ፡-
- ዶክተር ምህረት ደበበ…ከአፍሪካ የአመራር ልቀት አካዳሚ….ሰብሳቢ
- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት……ከጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት…አባል
- አቶ ማዕረጉ በዛብህ………የሚዲያ ባለሞያ……..አባል
- ዶክተር ነገሪ ሌንጮ…….ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት…….አባል
- ወይዘሮ ሃና አርአያ ስላሴ…..ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት…..አባል
- አቶ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ…..የግል ስራ…..አባል
- ረ/ፕ መኩሪያ መካሻ..ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ…አባል
- ወይዘሮ ነብያት መሃመድ…….ከስራና ክህሎት ሚኒቴር…አባል
- ዶክተር ከይረዲን ተዘራ……ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት…አባል