በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በአሜሪካ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በአሜሪካ ሊካሄድ ነው
ኢዜአ ጥቅምት 29 ቀን 2015 በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር የፊታችን ቅዳሜ ሕዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም በአሜሪካ ይካሄዳል።
ዝግጅቱ “ለሀገራዊ ጥሪ ወገናዊ ምላሽ” በሚል መሪ ሀሳብ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደሚከናወን ኢዜአ ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ግብረ ኃይል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ሳቢያ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖቹ ድጋፍ በማድረግ ሰብአዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለባቸው ገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ በአካል መገኘት የማይችሉ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት የገንዘብ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በከፈተው 1000439142786 ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ የሂሳብ ቁጥር እና በ'አይዞን ኢትዮጵያ' የኦንላይን የገንዘብ ክፍያ አማራጭ ድጋፉን ማድረግ እንደሚችል አመልክቷል።
በመርሐግብሩ ላይ የመንግስት ተወካዮች፣አርቲስቶች፣ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያውንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ግብረ ኃይል ከተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል።