ቀጥታ፡

አራተኛው የኢትዮ-ካናዳ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በቶሮንቶ ተጀመረ

ጥቅምት 29/2015(ኢዜአ) አራተኛው የኢትዮ-ካናዳ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በካናዳ ቶሮንቶ ተጀምሯል።

በፎረሙ ላይ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እና የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ እየተሳተፉ ነው።

በመንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት እንዲሁም የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች የለውጥ ስራዎች የፈጠሯቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች አስመልክቶ ለካናዳ ባለሀብቶች መረጃ ለመስጠት ፎረሙ መዘጋጀቱን አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል።

ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ በማዕድን፣በግብርና ማቀነባበሪያ፣ቱሪዝም፣በቴክኖሎጂና አምራች ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ፎረሙ የካናዳ ባለሀብቶች የኢትዮጵያ ምርቶች እንዲገዙ እንዲሁም የኢትዮጵያና ካናዳ ባለሀብቶችና አምራቾች ትስስር እንዲፈጥሩ ከማድረግ አኳያ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

ትላንት በተጀመረው በዚህ ፎረም ላይ የኢትዮጵያና ካናዳ ግንኙነት በንግድ ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር መደረጉን አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባሏት የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች ዙሪያ ገለጻ የተደረገ ሲሆን ፎረሙ ዛሬ ይጠናቀቃል።

ሶስተኛው የኢትዮ-ካናዳ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም እ.አ.አ በ2018 በካናዳ ቶሮንቶ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያና የካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ 1965 መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም