ቀጥታ፡

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ቀን በመጪው ህዳር 10ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢዜአ):በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ቀን በመጪው ህዳር 10ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባቸው ሃገራት አንዱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ነው።

በየአመቱም በአቡዳቢ እና ዱባይ አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበትን የኢትዮጵያዊያን ቀንን የሚያከብሩ ሲሆን ዘንድሮም በመጪው ህዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተጠናቀቀ ይገኛል ።

ቀኑ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች የሚከበር ሲሆን ባህል እና የተለያዩ ኪናዊ ሁነቶችን ጨምሮ በሃገራቸው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምክክር በማድረግ ጭምር ይከናወናል።

ዝግጁቱን አስመልክቶ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ እንዳሉት በአረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ መልኮች ሳያቋርጡ ሃገራቸውን እያገዙ ይገኛሉ።

በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና በሃገር አንድነትና ሉአላዊነት ረገድ ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያውያን ቀን የሚከበረው የሰላም ስምምነት በተፈረመ ሰሞን መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ሱሌማን ፤ በዓሉ ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያኑ ለሃገር መልሶ ግንባታ በሚኖራቸው ቀጣይ አስተዋፅኦ እንደሚመከርበትም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ በቀጣይም ባካበቱት እውቀት እና ባላቸው ሃብት ሃገራቸውን እንዲያለሙ ለማድረግ ኤምባሲው እየሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ዘንድሮ በሚካሄደው የኢትዮጵያውያን ቀን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም