የመንገድ ዳር ምልክቶችንና የኤሌክትሪክ ገመዶችን በመስረቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

168

ሰቆጣ፤ ጥቅምት 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) የመንገድ ዳር ምልክቶችንና የኤሌክትሪክ ገመዶችን ሰርቀው በመሸሸግ ለማሳለፍ የሞከሩ ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች መያዙን በሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት መነሻቸውን ጋዝጊብላ ወረዳ በማድረግ ባገለገሉ ቁሳቁሶች ውስጥ ሸፍነው በመሸሸግ  ለማለፍ ሲሞክሩ ብልባላ ከተማ አቅራቢያ ኬላ  ዛሬ በተደረገ ፍተሻ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ተገኘ ወርቁ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-  79350 አአ የሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ የመንገድ ዳር ምልክቶችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ከነተጠርጣሪዎቹ መቆጣጠር መቻሉን  አስታውቀዋል።



ከእነዚህም  ውስጥ በውድ ዋጋ ከውጭ የገቡ ለብልባላ-ሰቆጣ የአስፓልት ስራ ፕሮጀክት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ በርካታ የመንገድና የፍጥነት መጠቆሚያ ምልክቶች መሆናቸውን  ምክትል ኮማንደሩ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ገመድ ፣የትራንስፎርመር ተሸካሚ ብረትና አዲስ  የውሃ  ቱቦዎች መገኘታቸውንም አስረድተዋል።

በድርጊቱ የተጠረጠሩ አሽከርካሪውንና ሌላ ግለሰብ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ባገለገሉ ቁሳቁሶች ንግድን ሽፋን በማድረግ የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን የሚያወድሙ ግለሰቦች ህብረተሰቡ አጋልጦ ለህግ አሳልፎ በመስጠት ትብብሩን  እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም