የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ ዛሬ ይካሄዳል

759

ጥቅምት 29/ 2015 (ኢዜአ) 23ኛው የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ(ሚድ ተርም ኢሌክሽን) ዛሬ ይካሄዳል።

ለአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት (ኮንግረስ) 435 መቀመጫዎችና ከአስፈጻሚው (ከሴኔቱ) 100 መቀመጫዎች ውስጥ 34ቱ (አንድ ሶስተኛው) ለምርጫ ይቀርባሉ።

በምርጫው የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠብቃሉ ያላቸውን  28 የሴኔትና ኮንግረስ እጩዎች(ሪፐብሊካንና ዴሞክራት ፓርቲ) ይሁንታ (ኢዶርሰመንት) መስጠቱን ኢዜአ ከ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’(ኤፓክ) የተሰኘው የፖለቲካ ተግባር ኮሚቴ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በተጨማሪም ለግዛት አስተዳዳሪነትና ለከንቲባነት እንዲሁም ማዘጋጃ ቤታዊ (City council) እና አውራጃ (County) ምርጫ ለሚወዳደሩ 13 እጩዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

እጩዎቹ እውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲን መሰረት በማድረግ ሳይሆን የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያጠናክራሉ በሚል እምነት እንደሆነ  አመልክቷል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎችን ታሳቢ በማድረግ በ21 ግዛቶች ብሔራዊ የምርጫ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሲሰሩ ቆይተዋል።

እጩዎችን የመምረጥና የመወሰን መብት የመራጮች ቢሆንም ተወዳዳሪዎቹ የማሸነፍ እድላቸው የተሻለ የሚባል  እንደሆነ ነው ኤፓክ ያስታወቀው።

ድጋፍ የተሰጣቸው እጩዎች ቢመረጡ በአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ደጋፊ ስብስብን (ኮከስ) ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጿል።

ኤፓክ መምረጥ የሚችሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምርጫው ቀን ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ(ሚድ ተርም ኢሌክሽን) በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ነው።

በኮንግረስ ምርጫ የሚያሸንፍ እጩ ለሁለት ዓመት እንዲሁም የሴኔት ተወዳዳሪ ለስድስት ዓመት ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም