ቀጥታ፡

አፍሪካ ባላት እምቅ የተፈጥሮ ኃብት ልክ እንድታድግ የአፍሪካውያን የእርስ በእርስ ግንኙነት ሊጠናከር ይገባል-ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ጥቅምት 29 /2015 (ኢዜአ) አፍሪካ ባላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ልክ እንድታድግ የአፍሪካውያን የእርስ በእርስ ግንኙነት የበለጠ ማደግ እንዳለበት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 6ኛው የአፍሪካ ኢንጂነሪንግ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ፕሬዝዳንቷ እንዳሉት የመሰረተ ልማት ፍላጎትና አቅርቦት በፍጥነት እያደገ ነው።

አፍሪካ መልማትና መበልጸግ የሚያስችላት የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም ተባብሮ መስራት አለመቻል ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

አህጉሪቱ ያላትን እምቅ አቅም መጠቀም ትችል ዘንድ በአፍሪካውያን መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነቱ ከዚህ በላይ ማደግ እንዳለበት ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኢንጂነሮች ጉባኤ አፍሪካን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ጉልህ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ይህ አይነቱ ምክክር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ጉባኤው በኢንጂነሮች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠር የአፍሪካን የመሰረተ ልማት ግንባታ ፈጣንና ጥራት ያለው እንዲሆን ያግዛል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም