ቀጥታ፡

አርቲስት አሊ ቢራ ለጥበብ ጎህ የቀደደ፣ ለወጣቶች አርዓያ ሆኖ ያለፈ ታላቅ ድምጻዊ ነው - የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2015/ኢዜአ/ አርቲስት አሊ ቢራ ለጥበብ ጎህ የቀደደ፣ ለወጣቶች አርዓያ ሆኖ ያለፈ ታላቅ ድምጻዊ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ ተናገረ፡፡

አርቲስት አሊ ቢራ የአስክሬን ሽኝት በወዳጅነት አደባባይ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የሙያ አጋሮች፣ አድናቂዎቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡

የኢትዮጵያ  ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር"አሊ ቢራ ከጥበብ ባህር ጨምቆ ያወጣቸውን ድንቅ ስራዎች ለህዝብ ያበረከተ አርቲስት ነው" ብሏል።

ለወጣቱ ትውልድ መንገድ ያሳየ እና ለጥበብ ጎህ የቀደደ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

አርቲስት ዓሊ ቢራ ባለፉት 60 ዓመታት በሰራቸው ስራዎች ስለፍቅር፣ አንድነትና ነጻነት አቀንቅኗል፤ በዚህም የጥብበን ታላቅነት አሳይቷል  ነው ያለው፡፡

በዚህም አርቲስት አሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ባለውለታ መሆኑን ጠቅሶ፤ አርቲስቱ ከእራሱ አልፎ ለበርካታ ድምጻዊያን የጥብበ ስራዎችን በማበርከት አርአያነት ያለው ስራ ማከናወኑን ተናግሯል፡፡

አርቲስቱ ደግና ሰው ወዳድ እንደነበርም ነው የተናገረው፡፡

የኦሮሞ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት  ጸጋዬ ደንደነ በበኩሉ አርቲስት አሊ ቢራ በስራዎቹ አንድነት፣ ነጻነትንና እኩልነት እንዲሰፍን መስራቱን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም