የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቅና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ገዳም ልትገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቅና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ገዳም ልትገነባ ነው
ጥቅምት 28/2015 /ኢዜአ /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቅና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ገዳም ልትገነባ ነው፡፡
ለገዳሙ የሚሆነውን ቦታ ለመግዛት የተቋቋመው ኮሚቴ ከቤተክርስቲያኗ አባቶች ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ፣ የኔቫዳና አሪዞና አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ዶክተር አቡነ ቴዎፍሎስ በዚሁ ጊዜ፤ ገዳሙ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው ብለዋል
ቦታውን በውስጡ ካሉት ንብረቶች ጋር ለመግዛት በአጠቃላይ 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ እስካሁን ባለው ሂደት ከ400 ሺህ ዶላር በላይ የቅድመ ክፍያ መፈጸሙን ጠቁመዋል፡፡
ቦታው ከ1 ሺህ 497 ሔክታር በላይ ይዞታ እንዳለውና የተለያዩ መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ሊሰጥባቸወ የሚችሉ አራት ዘመናዊ ቤቶች ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ በግቢው ውስጥ በዓመት ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኙ ከ100 በላይ የቀንድ ከብቶችና ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ የጭነት፡ የእርሻና የቤት ተሽከርካሪዎችም ይገኙበታል፡፡
ለተለያዩ ግንባታዎች የሚውሉ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችን ያካተተ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ፤ በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኘው ይህ የገዳም ቦታ ያለው ሃብት የእምነቱን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለመላ ኢትዮጵያዊያን አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አብራርቷል፡፡
ገዳሙ የሚሰጠው አገልግሎት ኢትዮጰያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስተዋውቅ ብሎም ፓንአፍሪካኒዝምን የሚያንጸባርቅ መሆኑንም ነው የተናገረው፡፡
በቀጣይ በገዳሙ ውስጥ ሆስፒታል፣ትምህር ቤቶች፣ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፣የእደ ጥበብ ውጤቶቸ መስሪያ ማዕከል፣ቤተ መጻህፍትን ጨምሮ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ 14 ማዕከላትን ለማቋቋም መታቀዱንም ተናግሯል፡፡
በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ ሃብቶችን ወደ ገቢ ምንጭነት በመቀየር ከቤተ ክርስቲያኗ ባሻገር የኢትዮጰያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ነው ያላቸውን እምነት የገለጸው፡፡
የእምነቱ ተከታዮችን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያዊያን ለቦታው ግዢ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል፡፡