የመንገድ ግንባታው በጉዞ ላይ የነበረባቸውን እንግልት እንዳስቀረላቸው አሽከርካሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ ግንባታው በጉዞ ላይ የነበረባቸውን እንግልት እንዳስቀረላቸው አሽከርካሪዎች ተናገሩ
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 በመንገድ ልማት ዘርፍ የተከናወኑት ተግባራት በጉዞ ላይ የነበረውን እንግልት እንዳስቀረላቸው አሽከርካሪዎች ተናገሩ። በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተካሔደው የመንገድ ግንባታ 26 ሺህ 550 የነበረውን የመንገድ አውታር ወደ 120 ኪሎ ሜትር ማድረስ መቻሉን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ገልጿል። ለ35 ዓመታት በአገር አቋራጭ አሽከርካሪነትና በረዳትነት ሲሰሩ የነበሩት አቶ በቀሌ ተክሌ ከ15 አመት በፊት ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መጓዝ የሚፈልጉ መንገደኞችን ለማድረስ መሰረተ ልማቱ እንደልብ የሚያስኬድ እንዳልነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ሳቢያ የሚፈልጉበት ቦታ ሳይደርሱ መኝታ ይዞ ማደር የግድ በመሆኑ ለአሽከርካሪውም ሆነ ለመንገደኞው ተጨማሪ ወጪና እንግልት ይፈጥር ነበር ብለዋል። አሁን ግን የመንገድ መሰረተ ልማቱ በመስፋፋቱ ያለምንም ውጣ ውረድ ረዥም መንገዶችን በሰዓታት ለማቋረጥ መቻሉን ነው ያብራሩት፡፡ ለ16 ዓመታት በላዳ ታክሲ አሽከርካሪነት ሙያ የሰሩት አቶ በኃይሉ ሽመልስም ይሕንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አሁን አሁን በተለይ መንገድ ግንባታ ላይ ጥሩ ለውጦች እየታዩ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ አካባቢ በፍጥነት ለመሔድና በተለይ ታማሚዎችን የሚፈልጉት ቦታ ለማድረስ አዳጋች እንደነበር ያስታውሳሉ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከ300 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከ146 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገዶችን የማጠናከር፣ የደረጃ ማሻሻልና ማሳደግ እንዲሁም የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ተካሂዷል። እንደ አቶ ሳምሶን ገለፃ በ1990 ዓ ም በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የመንገድ አውታር 26 ሺህ 550 ኪሎ ሜትር ነበር። ከዚያ ወዲህ የተሰራው የልማት ስራ ከ120 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ደርሷል፡፡