ቀጥታ፡

በቀጣይ አንድ ወር አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ደረቅ፣ ፀሀያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ አመዝኖ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አባባ  (ኢዜአ) ጥቅምት 28/2015 በቀጣይ አንድ ወር በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ደረቅ፣ ፀሀያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ አመዝኖ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በጥቂት ደጋማ ቦታዎች የሚጠበቀው ውርጭ የደረሱ ሰብሎችን እንዳይጎዳ አርሶ አደሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ኢንስቲትዮቱ አሳስቧል።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የበጋ ደረቅ፣ ፀሀያማ እና ነፋሻማ  የአየር ሁኔታ አመዝኖ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በአንዳንድ ደጋማ የአገሪቱ ቦታዎች እየተስተዋለ የሚገኘው የሌሊት እና የማለዳ ቅዝቃዜ ከወሩ አጋማሽ በኋላ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችልም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የአየር ጠባይ አዝማሚያው አልፎ አልፎ ከሚኖረው የደመና ሽፋን ጋር ተያይዞ እስከወሩ አጋማሽ ድረስ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ በደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብና በደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ይኖራል ተብሎ እንደሚጠብቅም እንዲሁ።

የሚቀጥሉት ወራቶች የመኸር ሰብል አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች ሰብሎች ለፍሬ የሚበቁበትና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ሰብሎች የእድገት ጊዜያቸውን ጨርሰው ለመሰብሰብ የሚደርሱበት ወር ነው።

በደቡብ ምዕራብና የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች መጠነኛ የሆነ እርጥበት የሚያገኙበት ወር መሆኑንም የአየር ትንበያ መረጃው ያሳያል።

በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሀያማና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ማመዘኑንም ሰብል ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተመላክቷል፡፡

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚጠበቀው የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በጥቂት ደጋማ ቦታዎች በሚጠበቀው ውርጭ የደረሱ ሰብሎችን እንዳይጎዳ አርሶ አደሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም  ኢንስቲትዮቱ አሳስቧል።

የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንደየ አካባቢው ሁኔታ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንዳለባቸውም ነው መግለጫው የጠቆመው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖረው ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ዘግይተው ለተዘሩ የመኸር ሰብሎች የውሃ አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላት፣ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በአብዛኛው የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ የበጋ ደረቅና ፀሃያማ ሁኔታ የሚያመዝን ሲሆን በደቡብ ምዕራብና ደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ተፋሰሶች ከመጠነኛ እስከ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖርም ተጠቁሟል።

ከዚህ አኳያ ባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ፣ የመካከለኛው እና የታችኛው ኦሞ ጊቤ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ የታችኛው ስምጥ ሸለቆ እና ኦጋዴን ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

የተቀሩት የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ ደረቅ እና ከፊል ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝንም ነው ኢንስቲትዮቱ ያመላከተው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም