አሊ ቢራ - የጸደይ ብርሃን አብሳሪ - ኢዜአ አማርኛ
አሊ ቢራ - የጸደይ ብርሃን አብሳሪ
(በአሸናፊ በድዬ)
"ሰምቼ የማልጠግበው ድምጽ 'ዛሬ ዝም አለ' የሚል ዜና ሰማሁ። እንደሌላ ጊዜው ውሸት በሆነ ብዬ ተመኘሁ። ግን መራራ እውነት ነው። ባለወርቃማ ድምጹ አሊ ቢራ ትቶልን የሄደው ብዙ ነው።" ይህ አንድ የአንጋፋው አርቲስት አድናቂ ሀዘኑን የገለጠበት መንገድ ነው።
እውነትም ክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከሙዚቃ ጋር ከስድስት አስርታት የበለጠ እድሜ የተቆራኘ መጠሪያውን ጭምር በጥበብ ስራው የተካ ድንቅ ሰው ነበር።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑ አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ይመደባል።
በተለይም የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃዎች ከፍ ብለው እንዲደመጡና በርካታ ሰዎች ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር አሊ ቢራ የነበረው ሚና እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡
ሙዚቃ ቋንቋ ነው የሚለውን ብሂልም በተግባር አሳይቷል። ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በበርካታ ቋንቋዎች ሙዚቃን የሚጫወተው አሊ ቢራ በአፋን ኦሮሞ በተጫወታቸው በርካታ ሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን በመቻሉ ትልቅ ስፋራ ይሰጠዋል፡፡
ይህ የሙዚቃ ሰው በድሬደዋ ገንደ ቆሬ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ከአባቱ መሐመድ ሙሳ እና ከእናቱ ፋጡማ አሊ በ1940 ዓ.ም ነው የተወለደው።
ከህጻንነቱ ጀምሮም የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን እያደመጠና እያንጎራጎረ ማደጉ ይነገራል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካ አገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርት ተምሯል።
አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም ገና በ13 ዓመቱ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ አድረጎ የተቋቋመውን ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነው የሙዚቃ ስራውን አንድ ብሎ የጀመረው።
አሊ ቢራ በዚህ የባህል ቡድን ተቀላቅሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ያቀነቀነው ሙዚቃም የዛሬው የስሙ መጠሪያ የሆነው "ቢራ ዳ በሪኤ" የሚለው ሙዚቃ ነው፡፡
"ቢራ ዳ በሪኤ" የሚለው ሙዚቃ ከባዱ ክረምት አልፎ አዲስ ብርሃን መውጣቱን ገና በለጋ እድሜው በማብሰር የሙዚቃ ተስፋውንም አብሮ ያለመለመበት ነው።
በዚህ ሙዚቃ ምክንያትም "አሊ መሐመድ ሙሳ" የነበረው ስሙ "አሊ ቢራ" ተብሎ እንዲጠራ አድርጎታል፡፡
ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በሃረሪ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች የመዝፈን ችሎታ አለው።
በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት የሰራ ሲሆን ‘አይቤክስ’ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ስራዎቹን በዲ አፍሪካ ሲያቀርብ መቆየቱም ይነገራል፡፡
ከ267 በላይ ሙዚቃዎች ያበረከተው ድምጣዊው በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን አልበሙን በ1971 ዓ.ም ከመስራቱ በተጨማሪ ለገበያ የቀረቡ 13 አልበሞች እንዳሉትም በአንድ ወቅት ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡
የክብር ዶክተር አሊ ቢራ የሙዚቃ ስራዎች አፋን ኦሮሞ በማይሰሙ ሰዎች ዘንድም ጭምር እጅግ ተቃባይነት ያላቸው መሆኑን ባለቤቱን ጨምሮ በርካቶች ምስክርነት ሰጥተዋል።
እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ስራዎቹ መካከልም:- "Birraa dhaa Barihe" የመጀመሪያ ስራው፣ " Waa Malli nu dhibe"፣ "Jaalaluma teeti"፣ "Barnootaa"፣ "Ushuruururuu"፣ "Karaan Mana Abbaa Gadaa"፣ "Nin deema"፣ "Dabaala Keessan" የሰርግ ሙዚቃ፣ "Amalele" ከብዙዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ድምጻዊ አሊ ቢራ "Waa Malli nu dhibe" በሚለው የሙዚቃ ስራው እናታችን አንድ ናት ምንድነው የሚያለያየን በማለት ኢትዮጵያዊያን አንድ መሆናቸውን እና መቼም መለያየት የማይችሉ የአንድ እናት ልጆች መሆናቸውን በሙዚቃ ስራው በማቀንቀን ከመለያየት ይልቅ አንድነት ፍቱን መፍትሄ መሆኑን አንጸባርቆበታል፡፡
"Karaan Mana Abbaa Gadaa" በሚለው የሙዚቃ ስራውም ፍትሃዊነት፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ መልካምነት፣ ግልፀኝነት፣ ሀቀኝነት የገዳ ስርዓት መገለጫዎች ስለመሆናቸው አቀንቅኗል፡፡
"ትምህርት የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ ነው" ብሎ እንደሚያምን የሚናገረው ድምጻዊ አሊ ቢራ ትውልዱ ትኩረቱን ትምህርት ላይ ብቻ ማድረግ እንዳለበትም "Barnootaa ammas Barnootaa" በሚለው ሙዚቃ ስራው አስተምሯል፡፡
"Amalele ……….. an yaada keen takka hin bule" በማለት ስለፍቅር ሃያልነት ባቀነቀነው ሙዚቃ ፍቅር የሁሉም ነገር ማሰሪያ፣ ከደስታዎች ሁሉ በላይ ደስታ መሆኑም ለትውልዱ አስተምሯል፡፡
ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የተለያዩ ፈተናዎችን ተሻግሮ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት ያደርገዋል።
በርካታ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወተው አሊ ቢራ ከአርባ በላይ በሆኑ አገራት እጅግ በርካታ የመድረክ የሙዚቃ ስራዎችን ተጫውቷል።
ባለፉት 60 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ እንቁ ሆኖ የቆየ፣ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት የቻለ፣ ትውልዱ በእውቀት እና በስነ-ምግባር እንዲቀረጽ በሙዚቃ ስራው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ነው፡፡
ድምጻዊ ዓሊ ቢራ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁመው ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በዘርፉ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ ሁለት የክብር ዶክተሬት የተሰጠው አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችን አግኝቷል።
ለአብነትም ከድሬዳዋ እና ከጅማ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል፤ በድሬደዋ ከተማ ፓርክ እንዲሁም በአዳማ መንገድ በስሙ ተስይሟል፣ የኦሮሚያ ክልል በሙዚቃው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ልዩ የኒሻን ሽልማት አበርክቶለታል፤ የመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ተሸላሚም ሆኗል፤ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የኪነጥበብ ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከፍተኛ ሽልማት አግኝቷል፤ በካናዳ ቶሮንቶ የአፍሪካ የምንጊዜም አንጋፋ ሙዚቀኛ ሽልማት አግኝቷል፤ የኦዳ አዋርድ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ መሆን ችሏል፤ ሌሎችንም ከፍተኛ ማዕረጎችንና ሽልማቶች አግኝቷል፡፡
የአንጋፋውን አርቲስት የክቡር ዶክተር አሊ ቢራን ህልፈት ህይወት አስመልክቶ ብዙዎች ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሙያ አጋሮቹ አገር ትልቅ ባለውለታዋን ማጣቷን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ "የአንጋፋው ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ህልፈት ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው፤ በዜማዎቹ ኅብረትን፣ ጽናትንና ባህልን አቀንቅኗል፤ ለብዙዎችም አርአያ ሆኗል፤ ላደረግከው ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግንሃለች" በማለት ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ይህ አንጋፋ አርቲስት በህይወት ቢለየንም ህያው ስረዎቹ ግን አብረውን ይዘልቃሉ።