የሰላም ስምምነቱ በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል -ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

159

ደሴ ( ኢዜአ ) ጥቅምት 28/2015 በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ አስገነዘቡ ።

በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉና ጃማ ወረዳዎች በክላስተር የለማ ስንዴ ጉብኝት ተካሄዷል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳሉት በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያሽነፉበትን እድል ፈጥሯል ።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የምታረጋግጥበትና ሙሉ በሙሉ ፊቷን ወደ ልማት የምታዞርበት መሆኑን አመልክተዋል።

ስምምነቱ በሃገሪቱ አዲስ ምዕራፍ የታየበት ነው" ሲሉም አመልክተዋል።

የሰላም ስምምነቱ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ በመሆኑ ለውጤት እንዲበቃ ከሃሳብ ጀምሮ በስራ ጭምር በመደገፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በውስጣችን ያሉ ችግሮችን በውይይትና በምክክር ልንፈታ ይገባል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር ናቸው።

በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል ።
የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን አሽናፊነት ያረጋገጠ መሆኑን ያመለከቱት  ዶክተር ጌታቸው ስምምነቱ "ለክልላችን ህዝብ  ጨምሮ ለመላው ኢትዮጵያዊ ታላቅ የምስራች ነው" ብለዋል።

የተደረሰው ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን ከአፍራሽ ሃሳቦች በመራቅ መተጋገዝና መደጋገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም