ከሰሜን ሸዋ ዞን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ628 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

83
ደብረ ብርሀን ግንቦት11/2010 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል ከተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ628 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን በአማራ ክልል ሰሜን የሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የእቅድ ዝግጅትና ክትትል ባለሙያ አቶ ጌትዬ አያልቅበት ለኢዜአ እንደገለጹት ገቢው የተሰበሰበው ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ሩጫ ከተዘጋጀ ቲሸርት ሽያጭ ነው ። ቲሸርቱ በዞኑ 24 ወረዳዎች ለህብረተሰብ  ተከፋፍሎ በመሸጥ ድጋፉ ተገኝቷል፡፡ "የህዳሴ ግድቡን ምክንያት በማድረግ በሚደረገው ሩጫ በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነዉ" ብለዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህል ፣ቱሪዝም፣ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ማሞ በበኩላቸው በከተማው በተካሄደው የቲሸርት ግዥ ላይ የመንግስት ሰራተኞች፣ነጋዴዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በከተማው የቀበሌ ስድስት ነዋሪ አቶ አያሌው  በለጠ የህዳሴው ግድብ ሩጫ ላይ ለመሳተፍ ቲ-ሸርት መግዛታቸውን ተናግረዋል ። ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ በሶስት ዙር የ7ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን የገለፁት አቶ አያሌው ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ። ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተዘጋጀው ሩጫ ግንቦት 19 ቀን 2010 አ.ም በደብረብርሀን ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም