ቀጥታ፡

የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች በክቡር ዶክተር ዓሊ ቢራ ህልፈት-ህይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 28 ቀን 2015 የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በህዝብ ልብ ዉስጥ ለዘመናት ነግሶ በቆየው በክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ህልፈት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም እየገለጽኩ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ፣ ለአድናቂዎቹና ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ ብለዋል።

ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በትላንትናው እለት በሞት መለየቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተደድር ሽመልስ አብዲሳ በአርቲስቱ ህልፈት የተሠማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በመግለጫቸው አርቲስት ዓሊ ቢራን "ባለ ድምፀ መረዋ፣ ሁለገብ የሙዚቃ መሠረት" ሲሉት አርቲስት ዓሊ ቢራን ማጣት መሪር ሀዘንን ፈጥሮብናል ብለዋል።

ኖሮ ማለፍ ላይቀር እንደ ዓሊ ቢራ የክብር ካባ ለብሰው ለሰው ልጆች ደስታ ሰርተው ያለፉ ግን ጥቂት ናቸው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክብር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ እረፍት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሀዘን መልክት በአርቲስት ዓሊ ቢራ ሕልፈት ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አርቲስት አሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ጥበብና ስልጣኔ እደገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተ ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድ አርአያ ሆኖ ያለፈ ድንቅ አርቲስት ነው ሲሉም አክለዋል።

አሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝብ መቻቻልንና አብሮነትን፣ ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክሩ በርካታ የጥበብ ስራዎችን ተቀኝቷል፤ አቀንቅኗል፤ ለህዝብ አበርክቷልም ብለዋል በመልዕክታቸው።

በዚህም በአንጋፋው አርቲስት አሊ ቢራ ህልፈት ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በክልሉ መንግሥት ስም ገልጸው፤ ለቤተሰቦቹ፣ወዳጅ ዘመዶቹና ለጥበብ አድናቂዎቹ በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት አርቲስት ዓሊ ቢራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የማይጠፋ የሀገር ባለውለታ መሆኑን አንስተዋል።

አርቲስት አሊ ቢራ በኪነ ጥበብ ስራዎቹ ፍቅርን፣ መተሳሰብን አንድነትን ለመላው ህዝባችን በማስተማር ዘመን የማይሽረው የጥበብ አሻራውን ያሳረፈ ታላቅ ባለውለታችን ነበር ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በክቡር አርቲስት ዶክተር አሊ ቢራ ህልፈተ ህይወት ምክንያት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል፡፡

ቢሮው ዛሬ ለኢትዩጵያ ዜና አገለግሎት በላከው የሀዘን መግለጫ እንዳመለከተው አገራችን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የጥበበ ባለሙያዎች ድንቅ የሆነው ክቡር አርቲስት ዶክተር አሊ ቢራ ትላንት ማታ ማጣታችን ልብ ነክቶናል ብለዋል፡፡

ክቡር አርቲሰት ዶክተር አሊ ቢራ ከሙዚቃዎቹ ባሻገር ለአገር እና ለወገን የነበረው ፍቅርና ያሳየው ክብር መቼም የሚረሳ እንዳልሆነ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በደረሰው ድንገተኛ ሞት የክልሉ ህዝብ ለቤተሰቡ፣ለሙያ አጋሮቹ፣ለጓደኞቹና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም