በኤሌክትሪክ አገልግሎት የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራሁ ነው-አገልግሎቱ - ኢዜአ አማርኛ
በኤሌክትሪክ አገልግሎት የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራሁ ነው-አገልግሎቱ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 28 ቀን 2015 በኤሌክትሪክ አገልግሎት የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በአገልግሎቱ የቀጣይ 3 ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የሚመክር ሃገር አቀፍ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ፎረም እየተካሄደ ነው።
የአገልግሎት አሰጣጡን ተወዳዳሪና ደንበኛ ተኮር ለማድረግ የሚያግዘውና ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር አዲስ ስትራቴጂ እያስተዋወቀም ይገኛል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ አገልግሎቱ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት የለውጥ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል።
በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት መስጠት ላይ እየተሰራ መሆኑ ጠቁመው የጸሀይ በመጠቀም ሃይልን ተደራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።
ከኔትወርክ ማሻሻያ ጋር በተያያዘም በክልሎች የኔትወርክ ማስፋፊያ ተግበራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተከልሶ ወደ ስራ መገባቱን አብራርተዋል።
የኤሌክሪክ አገልግሎት ለህዝቡ በአስተማማኝ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዘርፉ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ዋና ስራ አስጻሚው በዚህ ዙሪያ ተቀናጅተን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
ሀገራዊ ፎረሙ እየተካሄደ ያለው በአዲስ አበባ ሲሆን በመድረኩ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን የበላይ ኃላፊዎች እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የኮሙዩኒኬሽን አመራሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን መረጃው ጠቁሟል፡፡