ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በትብብር ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ ለመውሰድ ትውልዱ ታላላቅ አሻራዎችን እያኖረ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጥቅምት 27/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያን በትብብር ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ ለመውሰድ ትውልዱ ታላላቅ አሻራዎችን እያኖረ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

አዲስ አበባ በዓለም አደባባይ ደምቃ እንድትታይ ላደረጉ አካላት በሚሊኒየም አዳራሽ የምስጋና እና የእውቅና ስነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

በስነስርዓቱ ላይም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የውጭ አገራት አምባሳደሮች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምስጋና እና እውቅና መርሃግብሩ ወቅት ሽልማቱን በጀመርነው የብልጽግና ጉዞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር ለማፅናት የምንጠቀምበት ይሆናል ብለዋል።

አባቶቻችን ነፃነቷን ጠብቀው ያስረከቡንን አገር፤ በትብብር ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ ለመውሰድ ትውልዱ ታላላቅ አሻራዎችን እያኖረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አሻራችንን የምናኖረው ወቅታዊ ችግሮችን ለማለፍ ብቻ አይደለም ያሉት ከንቲባዋ፤ መስራት እንደሚያስከብርና ለህሊናም እርካታ እንደሚሰጥ በማሰብ ጭምር ነው ብለዋል።

አገር የምትገነባው በስራና ጥረት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰራን ማመስገንና መሸለም ደግሞ ለበለጠ ምልካም ስራ እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።

መዲናዋ በተማሪዎች ምገባና ቆሻሻ አወጋገድ ባከናወነቻቸው ውጤታማ ተግባራት ሽልማት ማግኘቷ ትውልዱ ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ በመሸጋገር ታላላቅ አሻራዎቹን እያኖረ እንደሚገኝ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተገኘው የስኬት ሽልማትም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ እና በመዲናዋ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።

መዲናዋ ያሸነፈቻቸው ሽልማቶችም ለበለጠ ትጋት የሚያነሳሳና ሌሎች ታላላቅ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ ወኔ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለተማሪዎች እየቀረበ የሚገኘው የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ የሚማሩበት፣ ማቋረጥ የቀነሰበት፣ የውጤት መሻሻል የታየበት እና ወላጆችም ከብዙ ጭንቀት እፎይ ያሉበት ነው ብለዋል።

ይህም መንግስት የተለማቸው የትኩረት አቅጣጫዎችና ፖሊሲዎች ትክክለኛነት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ምስጋና አቅርበው፤ መዲናዋን እንደ ስሟ አበባ የማስመሰል ትጋታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የC-40 የአፍሪካ ሪጂናል ዳይሬክተር ሚስተር ሃስቲንግስ ቺኮኮ፤ "አዲስ አበባ እና ከንቲባዋ የC-40 ዓላማዎች ለማሳካት እያደረጉ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ለዚህ ዓለም አቀፍ እውቅና በመብቃቷ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፤ እውቅናውም የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት የታከለበት የተሻለ እርምጃ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በአገር ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያስጀመሩት "የሌማት ትሩፋት" መርሃግብርን በከተማዋ ተግባራዊ ለማድረግ በትጋት እንደሚሰራ ተገልጿል።

በስንዴ እና በአረንጓዴ አሻራ የተገኙ ውጤቶችን በእንስሳት ተዋጽኦ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በመድገም የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ርብርብ ይደረጋል ተብሏል።

አዲስ አበባ ብራዚል በተካሄደው ዓለም አቀፍ ፎረም በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምና በአርጀንቲናዋ ቦነሳይረስ በተካሄደው በC-40 የከንቲባዎች ፎረም በቆሻሻ አወጋገድ በተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች አዲስ የመልካም አርአያነት ግንባር ቀደም ተሸላሚ መሆኗ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም