የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አምራቾች ማበረታቻ እያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አምራቾች ማበረታቻ እያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ
ጥቅምት 27 2015 (ኢዜአ) ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካትና የአገር ውስጥ ምርትን ለማስፋት የኢንዱስትሪ ግብአት ለሚያመርቱ አምራቾች ማበረታቻ እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ ፈተና የሆነው የሸቀጦች ዋጋ መናርና የምጣኔ ሀብት ቀውስ በኢትዮጵያም ለዋጋ ግሽበት መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
መንግስት ችግሩን ለመፍታት ያስችላሉ ያላቸውን የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል፤ከነዚህ መካከል ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሪ አንገብጋቢ ለሆኑ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ ለመድኃኒቶችና የሕክምና መሳሪያዎች እንዲውል የተወሰነው ውሳኔ ይጠቀሳል።
በዚሁ መሰረት አስፈላጊነታቸው ዝቅተኛ የሆኑና ከውጭ የሚገቡ 38 ምርቶች የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ ገደብ መጣሉ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ መንግስት የወሰደው እርምጃ ባንኩ የያዘውን ዓላማ ከግብ እንዲያደርስ የሚያግዝ ነው።
ባንኩ ኢንዱስትሪዎችን በፋይናንስ ለመደገፍ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል የገቢ ምርቶችን መተካትና የወጪ ንግድ ላይ ማተኮር ዋነኞቹ መሆናቸውንና በዚህ ሂደት የሚያልፉ ምርቶች የበለጠ እንደሚበረታቱ ገልጸዋል።
ይህ ተግባር የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሪን ለመቆጠብ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና የአገርን እድገት ለማፋጠን ያግዛል ብለዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ ባንኩ በ2014 ዓ.ም በተመረጡ አካባቢዎች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም በሁሉም ክልል የትራክተርና ኮምባይነር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ባንኩ የወጪ ንግድን የሚያበረታቱና የገቢ ንግድን በሚተኩ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንና በተለይም በተመረጡ የግብርና ምርቶች ላይ ለሚያተኩሩና እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለሚሰሩ አካላት ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚያገለግሉ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ በአገር ውስጥ አምራቾች እንዲቀርቡ ለማድረግ ባንኩ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ባንኩ የገቢ ምርቶችን ለመተካትና የወጪ ምርትን ለማስፋት እንዲቻል የኢንዱስትሪ ግብአት ለሚያመርቱ አምራቾች ማበረታቻ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘይት፣ጥጥ እና ጨርቃጨርቅ አምራቾች የማበረታቸው ተጠቃሚ ከሚሆኑት መካከል ይገኙበታል፡፡
የግብርና ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ኢትዮጵያ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ማዋል እንደሚገባ ዶክተር ዮሐንስ አሳስበዋል፡፡