የቅመማ ቅመም ምርት የግብይት ስርአት ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የቅመማ ቅመም ምርት የግብይት ስርአት ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን
ጎንደር (ኢዜአ) ጥቅምት 27/2015 የቅመማ ቅመም ምርት የግብይት ስርአትን ያዘምናል ያለውን ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ከቅመማ ቅመም ምርት ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የልዑካን ቡድን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ በኩታገጠም እርሻ የለማ የበርበሬ ማሳን ትናንት ጎብኝተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የኢትዮጵያ ስነ ምህዳርና የአየር ጸባይ በአይነትና በብዛት እያደገ ለመጣው የቅመማ ቅመም ምርት ተመራጭ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 14 ሺህ ቶን የቅመማ ቅመም ምርት ወደ ውጪ በመላክ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ምርት በውጪ ገበያ እጅግ ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ "ሕንድ እና ፓኪስታን የዘርፉ ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ናቸው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የቅመማ ቅመም ዝርያዎች መኖራቸውንና በተለይም ዝንጅብል፣ ኮረሪማ፣ እርድ፣ በርበሬ፣ ነጭና ጥቁር አዝሙድ ግንባር ቀደም ተፈላጊ ናቸው።
በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለስልጣኑ የግብይት ስርአቱን ለማዘመን የግብይት ስትራቴጂ እያዘጋጀ እንደሆነ ዶክተር አዱኛ ገልጸዋል።
ይህም የሕገ-ወጥ ደላሎችን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት አምራቾችን በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል በ2014/15 የምርት ዘመን በበርበሬ ከለማው 76 ሺህ 800 ሄክታር መሬት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ ተወካይ አቶ ግዛት አብዩ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 30 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታገጠም በበርበሬ መልማቱንና የበርበሬ በሽታን የሚቋቋም የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በዞኑ በመኸር እርሻ በአምስት ወረዳዎች 32 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም መሸፈኑን ተናግረዋል።
ነጭና ጥቁር አዝሙድ፣በርበሬና ዝንጅብል በዞኑ እየለሙ ካሉ የቅመማ ቅመም አይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በመስክ ጉብኝቱ ላይ የባለስልጣኑ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ተመራማሪዎችን ጨምሮ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከደቡብና ከደቡብ ምዕራብ ክልሎች ግብርና እና ንግድ ቢሮዎች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።