ቀጥታ፡

ዘጠነኛው አገር አቀፍ የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄደ

ጥቅምት 27 ቀን 2015 (ኢዜአ) ዘጠነኛው አገር አቀፍ የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በቢሾፍቱ ከተማ ዛሬ ማለዳ ተካሄዷል።


በሴቶች አትሌት አፀደ ባይሳ ከኦሮሚያ ፖሊስ ስታሸንፍ አትሌት ፍቅርት ወረታ ከመቻልና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት ብዙአገር አደራ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በወንዶቹ ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቶች ፋንታሁን ሁነኛውና መኳንንት አየነው አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው ሲገቡ በግሉ የተወዳደረው አትሌት አብዱ አስፋው ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

በጎዳና ላይ ሩጫው በወንዶች ከ50 ዓመት በላይና በታች እንዲሁም በሴቶች ከ50 ዓመት በታች ውድድሮች ተካሄደዋል።

በወንዶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴት ኦሮሚያ ፖሊስ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የፌደሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ለውድድሩ አሸናፊዎች የገንዘብ እና የዋንጫ ሽልማት ማበርከታቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልፅዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም