ፍትህ ሚኒስቴር ለታራሚዎች የሚሰጡ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓቶችን እንዲፈትሽ ምክር ቤቱ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ፍትህ ሚኒስቴር ለታራሚዎች የሚሰጡ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓቶችን እንዲፈትሽ ምክር ቤቱ አሳሰበ

ጥቅምት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) በፍትህ ሚኒስቴር ለታራሚዎች የሚሰጡ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓቶችን እንዲፈትሽ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት እቅድና የመጀመሪያው ሩብ አመት አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው የተቋሙን የ2015 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት በምርመራ መዛግብት እቅድ አፈጻጸምና ሌሎች ተግባራት ላይ የተከናወኑ ስራዎችን አቅርበዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት የቀረበው እቅድና የሩብ አመት አፈጻጸም ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል።

የህግ የበላይነትን ከማስከበር፣ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ከማረጋገጥ፣ ከይቅርታ አሰጣጥ፣ ከሙስና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በስፋት አንስተዋል።
የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ መዛግብትን ከማጥራት፣ በአፋርና አማራ ክልሎች ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የተደረገውን ምርመራ በጥንካሬ አንስተዋል።
የታራሚዎች ይቅርታ አሰጣጥ ላይ በአቅም፣ በገንዘብ፣ እንዲሁም በዘመድ እንደሚሰጥ ቋሚ ኮሚቴው በማረሚያ ቤቶች ባደረገው ምልከታ ከታራሚዎች ቅሬታ እንደቀረበለት አንስተዋል።
ዋናው ወንጀል ፈጻሚ በይቅርታ ወጥቶ ተባባሪው ማረሚያ ቤት የሚቆይበት አሰራር እንደሚስተዋል ገልጸው ተቋሙ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓቶችን መፈተሽ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱ አስተያየቶችን በመውሰድ በቀጣይ የህግ የበላይነትን የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ሃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ጸጋ ከይቅርታ አሰጣጥ ጋር ቋሚ ኮሚቴው ያነሳቸው ችግሮች ቀደም ሲል የነበሩ መሆናቸውን በማመን በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ መሆኑን በሰጡት ምላሽ አንስተዋል።
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መርምሮ አስተማሪ ፍርድ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ተቋሙ እያከናወነ ያለው ተግባር ላይም ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል።
ፍትህ ሚኒስቴር የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብርን አጽድቆ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲያስገባም ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያ ሰጥቷል።