የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የአፍሪካና አውሮፓ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ምክክር እያካሄዱ ነው

278

ጥቅምት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የአፍሪካ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ጥምረት (ARUA) እና የአውሮፓ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች ጥምረት (Guild) የምክክር ጉባኤ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን እተካሄደ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲዎቹ እያካሄዱት ባለው ጉባኤ በተለይ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ላይ አጀንዳ አድርገው ተወያይተዋል፡፡

ጉባኤው የምርምር የልቀት ማእከላትን በቡድን ማቋቋምና ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በዚህም የደቡብ-ደቡብ (South-South) እንዲሁም የሰሜን-ደቡብ (North-South) ግንኙነትን ታሳቢ አድርጎ የሳይንስ ልህቀት ትብብር ስለመመስረት፣ የምርምር ልህቀት ማዕከላትን ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ነው ውይይት የተደረገው።

በውይይቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣት ተመራማሪዎች ሳይንሳዊ እድገትና የምርምር ክህሎት የሚያሳድግ፣ ለከፍተኛና መሪ ተመራማሪዎችም ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ከፍተኛ የምርምር ተቋማትን መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ተደራሽና አካታች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ተቋማትን በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ ማጠናከር የሚሉ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።

በድኅረ-ምረቃ (ማስተርስና ዶክትሬት ዲግሪ) ፕሮግራሞች የአውሮፓ- አፍሪካ ተማሪዎች ግንኙነትን ማጠናከር የሚሉ ጉዳዮች ከጉባኤው ተሳታፊዎች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም