መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ኢትዮጵያን የማጽናት ፕሮጀክት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ኢትዮጵያን የማጽናት ፕሮጀክት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
ጥቅምት 26/2015 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን የተሳሳቱ ትርክቶችን በማስተካከል ህዝብን ከህዝብ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ በትኩረት በመስራት ኢትዮጵያን የማጽናት ፕሮጀክት የማገዝ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር መሀመድ እድሪስን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች የኢዜአን የሚዲያ ልማት ስራ በጎበኙበት ወቅት ነው።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ ኢዜአ እያከናወነ የሚገኘው የሚዲያ የልማት ስራ ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር የሚያስችል ውጤታማ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱም ኢዜአ የገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከተቋሙ ባለፈ እንደ አገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጥና ለሌሎች የሚዲያ ልማት ስራዎችም ምሳሌ የሚሆን ነዉ ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሠ ቱሉ፤ ኢዜአ ቀደምትና ትኩስ መረጃን ለህዝብ ሲያቀርብ የቆየ አንጋፋ የመረጃ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በአገር ውስጥ ቋንቋ መረጃን ሲያቀርብ መቆየቱን ገልጸው፤ ተቋሙ የገነባው ዘመናዊ ስቱዲዮም የኢትዮጵያን ገጽታ ሊገነቡ የሚችሉ አጀንዳዎችን ቀርፆ ለመስራት የሚያስችል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
የህዝብ ልሳንናቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰራ ያለው የልማት ስራ ለበርካታ መገናኛ ብዙኃን ጥራት ያለው መረጃን ለማድረስ የሚያስችል መሆኑን እንደተገነዘቡም ገልጸዋል።
በፊልም ኢንዳስትሪና በማስታወቂያ ስራ የሚሰሩ አካላትም ኢዜአ የገነባቸውን ዘመናዊ ስቱዲዮዎች በመጠቀም ጥራት ያለው ስራ በማከናወን ገቢያቸውን ለማሳደግና ዓላማቸውን ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የጀመረውን የልማትና የመረጃ ተደራሽነት ስራ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን የሚያስተዋውቁ ሞጋች ጋዜጠኞችን ለማፍራት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ፤ ኢዜአ በሚዲያ ልማት እያከናወነ የሚገኘው ተግባር የሚያኮራ እንደሆነ በጉብኝታቸው እንደታዘቡ ገልጸዋል።
ተቋሙ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎችም ኢዜአ ከዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ቢሮ የሌላቸው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም የኢዜአን መሰረተ ልማት በመጠቀም ኢትዮጵያን የሚገልጹ መረጃዎችን ለዓለም ማድረስ የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
ይህን ማድረግ ሲችሉም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባትና በማስተዋወቅ ከፍተና አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።
መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማስተካከል ኢትዮጵያን የማጽናት ፕሮጀክት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተስፋ ጎዳና መራመድ በጀመረች ቁጥር ጫናዎች እንደሚበረቱባት ጠቅሰዋል።
የሚሰነዘሩባትን ጫናዎች ለመቋቋም ደግሞ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ማስተዋወቅ የሚችል መረጃን ለዓለም ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪኮች፣ የቱሪዝም ሃብቶችና የአብሮነት እሴቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የምትችልበትን ስርዓት የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተገልጿል።
እንደ ኢዜአ ያሉ አንጋፋ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም በአገር ውስጥ ከሚሰሩት ተግባር በተጨማሪ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማቅረብ እንዳለባቸው ተጠቁሟል።