ከስምምነቱ ማግስት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦንድ ሽያጭ በዓለም ደረጃ በፍጥነት ጨምሯል -አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ - ኢዜአ አማርኛ
ከስምምነቱ ማግስት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦንድ ሽያጭ በዓለም ደረጃ በፍጥነት ጨምሯል -አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ
ጥቅምት 26/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ከተደረገው የሰላም ስምምነት ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የኢትዮጵያ ‘ዩሮ ቦንድ’ ገዢ ኢንቨስተሮች ቁጥር በአንዴ በዓለም ደረጃ መጨመሩን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አመለከቱ።
በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን ለመገንባት የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ በተገቢው ከተተገበረ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አክለዋል።
ኢትዮጵያ የኢንቨስተሮች ፍሰትን ለመጨመር ከዓለም ኢንቨስተሮች የተበደረችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ‘ዩሮ ቦንድ’ በጦርነቱ ምክንያት ወደ አገሪቱ የመምጣት ፍላጎት በማጣታቸው የቦንዱ ዋጋ በዓለም ገበያ በጣም ቢወርድም ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ካላት ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ አብዛኛው በአምራች እድሜ ክልል መገኘቱና በአየር ንብረቷም በዓለም ኢንቨስተሮች ተመራጭ ሀገር ናት ያሉት አቶ ዘመዴነህ፤ የሰላም እጦቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ያስከተለው ጥቁር ጠባሳ እንዳለ ሆኖ አሁንም በዘርፉ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ መሰለፍ መቻሏን አስታውቀዋል።
የግድ ስለሆነ እንጂ ጦርነት የማንም ኢትዮጵያዊ ምርጫ አይደለም የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀውና መተኪያ የሌለውን የሰው ሕይወት ያጠፋውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ የጎዳውን ጦርነት በሰላም ከመቋጨት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም” ብለዋል።