ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
ጥቅምት 26/2015( ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ ጋር በሃገራቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በአቡዳቢ መወያየታቸው ተገለጸ፡፡
በውይይታቸውም በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተመላክቷል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አዘጋጅነት በሚገኘው የሰር ያሲ ባን ፎረም ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
በዋናነት ባሳለፍነው ሳምንት በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ገለፃ እንዳደረጉላቸው ተገልጿል።
መንግስት በዘላቂነት ሰላምን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እና ቱርክ ዘመንን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በውይይቱ ላይ የጠቀሱት አቶ ደመቀ በአሁኑ ወቅትም ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ተግባራት በተለያዩ መስኮች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት የሰላም ስምምነት በመፈረሙ የቱርክ መንግስት የተሰማውን ደስታ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጠናው መረጋጋት ጭምር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሀገራቸው መንግስት ድጋፍ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
ቱርክ በሁሉም መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።