የሬሚታንስ አላላክ ስርዓት ቀልጣፋና የመላኪያ ዋጋውም አነስተኛ እንዲሆን ሀገራት ህጎቻቸውንና አሰራሮቻቸውን ማጣጣም እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሬሚታንስ አላላክ ስርዓት ቀልጣፋና የመላኪያ ዋጋውም አነስተኛ እንዲሆን ሀገራት ህጎቻቸውንና አሰራሮቻቸውን ማጣጣም እንዳለባቸው ተገለጸ
ጥቅምት 26/2015 ( ኢዜአ) የሬሚታንስ አላላክ ስርዓት ቀልጣፋና የመላኪያ ዋጋውም አነስተኛ እንዲሆን ሬሚታንስ ተቀባይም ሆነ አመንጪ ሀገራት ህጎቻቸውንና አሰራሮቻቸውን ማጣጣምና ተቀናጅቶ መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ።
በቤልጂየም ብራስልስ "ሬሚታንስና ዘላቂ ልማት" በሚል መሪ መልዕክት ከፍተኛ የራባትና ካርቱም ፕሮሰስ መድረክ ከጥቅምት 24 እና 25 ቀን 2015 ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በኢትዮጵያ ዳያስፖራው ከሚልከው ሬሚታንስ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተቋማትና የግል ተዋናዮችን ሚና በተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
ከሬሚታንስ አላላክ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች፣ መጻኢ ዕድሎችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጨምሮ ሬሜታንስ በመላክ ሂደት ውስጥ እየፈጠሩ ስላሉ የዋጋ ቅናሽና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቀረቡ ጽሑፎች ላይ ውይይት መደረጉ ተመላክቷል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በቀረቡ ሀሳቦች ሬሚታንስ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳይ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በሀገራት መካከል ያለው የሬሚታንስ አላላክ ስርዓት ቀልጣፋና የመላኪያ ዋጋውም አነስተኛ እንዲሆን ሬሚታንስ ተቀባይም ሆነ አመንጪ ሀገራት ህጎቻቸውንና አሰራሮቻቸውን ማጣጣምና ተቀናጅቶ መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
የራባትና ካርቱም ፕሮሰስ በአፍሪካና የአውሮፓ አጋሮች መካከል እአአ በ2015 በተደረሰ ስምምነት የወጣውን የቫሌታ የድርጊት መርሃ ግብር ለማስፈጸም የሚዘጋጁ ከስደት ጋር የተያያዙ የውይይትና የቅንጅት መድረኮች ሲሆኑ፣ ትኩረቱም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ስደት በሚያገናኙ መስመሮች ላይ መሆኑን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።