ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

ጥቅምት 26/2015( ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ ጋር በአቡዳቢ መወያየታቸው ተገለጸ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ውይይት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመላክቷል።

በውይይታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ስለተፈረመው ስምምነት ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ያረጋገጡት አቶ ደመቀ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሁትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር ይበልጥ ደግሞ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በኢትዮጵያ በኩል እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎችም አብራርተዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ልዩ መሆኑን ጠቅሰው ግንኙነቱን በሚመጥን ደረጃ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም