ኤፓክ ለ28 የአሜሪካ የሕግ አውጪ ምክር ቤት እጩዎች ይሁንታ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ኤፓክ ለ28 የአሜሪካ የሕግ አውጪ ምክር ቤት እጩዎች ይሁንታ ሰጠ
ጥቅምት 26/2015(ኢዜአ) ‘የአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’(ኤፓክ) በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለ28 የሕግ አውጪ ምክር ቤት እጩዎች ይሁንታ (ኢዶርሰመንት) መስጠቱን አስታወቀ።
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ምርጫ ዘንድሮ ለ23ኛ ጊዜ የፊታችን ማክሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።
ለአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤት (ኮንግረስ) 435 መቀመጫዎችና ከአስፈጻሚው (ከሴኔቱ) 100 መቀመጫዎች ውስጥ 34ቱ (አንድ ሶስተኛው) ለምርጫ ይቀርባሉ።
‘የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ የተሰኘው የፖለቲካ ተግባር ኮሚቴ በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ብሔራዊ ቅስቀሳ በይፋ ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።
የኤፓክ የቦርድ አባል አቶ ፍስሀ አዱኛ ኤፓክ ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ መስራት እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የፖለቲካ ተግባር ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አጋሮቹ ጋር በመሆን አላማውን ያሳካሉ ያላቸውን እጩዎች የማነጋገርና የመለየት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
የልየታው ሂደት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴን ጨምሮ በኮንግረስና ሴኔት የሚገኙ ቁልፍ የሚባሉ ኮሚቴዎችን የያዙ ባለስልጣናትን ያማከለ እንደሆነም አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት ኤፓክ በማዕከል ደረጃ ይሁንታ (ኢንዶርስመንት) የሰጣቸው እጩዎች ቁጥር (ሪፐብሊካንና ዴሞክራት ፓርቲ) ከ16 ወደ 28 ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለግዛት አስተዳዳሪነትና ለከንቲባነት እንዲሁም ማዘጋጃ ቤታዊ (City council) እና አውራጃ (County) ምርጫ ለሚወዳደሩ 13 እጩዎች ድጋፍ ማድረጉን አቶ ፍስሀ ገልጸዋል።
እጩዎቹ እውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲን መሰረት በማድረግ ሳይሆን የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያጠናክራሉ በሚል እምነት እንደሆነ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ታሳቢ በማድረግ በ21 ግዛቶች ብሔራዊ የምርጫ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።
እጩዎችን የመምረጥና የመወሰን መብት የመራጮች ቢሆንም ተወዳዳሪዎቹ የማሸነፍ እድላቸው የተሻለ የሚባል እንደሆነ አመልክተዋል።
ድጋፍ የተሰጣቸው እጩዎች ቢመረጡ በአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ደጋፊ ስብስብን (ኮከስ) ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በምርጫው ከሚያሸንፉ እጩዎች ጋር በቀጣይ ስራዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግና በኤፓክ ይሁንታ ያላገኙ ነገር ግን ለኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ ከሚታመንባቸው ሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር በትብብር ለመስራት እቅድ መያዙን አመልክተዋል።
መምረጥ የሚችሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምርጫው ቀንና ከምርጫው በፊት ቀድሞ ድምጽ በሚሰጥባቸው ግዛቶች (Early voting) ድምጻቸውን እንዲሰጡ አቶ መስፍን ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚቴው በቀጣይ ተቋማዊ አቅሙን ማጠናከር፣ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አክለዋል።
እ.አ.አ በ2021 የቨርጂኒያ ገዢ ምርጫ በትውልደ-ኢትዮጵያውያን አና በኢትዮጵያ ወዳጆች ድምጽ ታግዘው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩው ግሌን ያንግኪን የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩን ቴሪ ማካውሊፍን አሸንፈው የግዛት ገዢ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።