ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የምትሰራውን የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትና የበለጠ አቅም መፍጠር ይገባታል - የተፋሰስ ባለሙያዎች

ጥቅምት 26/2015 /ኢዜአ/ ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የምትሰራው የአካባቢ ጥበቃ ስራ በወንዝና ውሃ አጠቃቀም ላይ ለሚፈጠሩ ቀጣናዊ ችግሮች መፍትሄ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትና የበለጠ አቅም መፍጠር እንዳለባት የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ባለሙያዎች ገለጹ።

ዓለም በሙቀት መጨመር፣ በበረሃማነት መስፋፋት፣ በዝናብ መጠንና ወቅት መዛባት፣ በድርቅ፣ በውቅያኖስ ውሃ መጠን መጨመር፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በሰደድ እሳትና ሌሎች መዘዞች እየተፈተነች ነው።

ለበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጋለጠው ምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ሳቢያ የገጠመው ፈተና 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' ሆኖበታል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ተፈጥሯዊ ሀብቶች የሕልውና ስጋት ላይ በመውደቃቸው ችግሩ እንዳይባባስ መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ስራን እንደ አንድ መፍትሔ ወስደዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ተቋም የሆነው የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ማህበረሰቡን ያሳተፈና የተቀናጀ የተፋሰስ ስራ ከሚሰራባቸው ስፍራዎች መካከል የጣና እና የዓባይ ወንዝ ተፋሰሶች ይገኙበታል።

በማዕከሉ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ባለሙያ ዶክተር አሰፋ ደርብ ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በተፋሰሱ ሰፋፊ ሰራዎችን እየሰራ ነው።

በዚህም አራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ በተፋሰሱ የሚሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር የጣና እና የዓባይ ተፋስስን በደለል ከመሞላት ለመጠበቅ ይበጃሉ ብለዋል።

በጣና ተፋሰስ መቶ በመቶ የአፈር መከላትን መጠበቅ ከተቻለ በየጊዜው የውሃ መጠንና ጥልቀቱ እየቀነሰ የመጣውን የጣና ሐይቅ መታደግ እንዲሁም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ከደለል መጠበቅ እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።

ከዚህም ባለፈ በተፋሰሱ የሚከናወኑ ስነ-አካላዊና ስነ ህይወታዊ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ከዓባይና ጣና ተፋሰስ ባሻገር በአየር ንብረት መዛባት ለተፈተነው ቀጣናው ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በማዕከሉ ሌላው የተፋሰስ ባለሙያ አቶ መለሰ ቢልልኝ በበኩላቸው በማዕከሉም ሆነ በሌሎች ተቋማት መሪነት በዓባይ ተፋሰስ የሚሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች የአየር ንብረት መዛባት ተፅዕኖን ለመቋቋም ያግዛሉ ብለዋል።

በተፋሰሱ በሚሰሩ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎችም ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት በአግሮ ኢኮሎጂ መስክ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል አንጋፋው ባለሙያ አቶ ወረታው አበራ ከ1970ዎቹ መባቻ ጀምሮ የዓባይ ተፋሰስ አካል በሆነው ጮቄ ተራራ በደን ሽፋን መጨመር ላይ በባለሙያነት በስፋት ሰርተዋል።

በወቅቱ በተሰሩ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ላይ አረንጓዴያማ ደኖች ሆነው ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ጥቅም እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ደን ጥበቃዎች ባሻገር የደን ሽፋን በመጨመር የገጸ ምደርና ከርሰ ምድር ውሃን ማጎልበት እንደሚቻል በየጊዜው የተሰሩ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን በአወንታ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በጣናና ዓባይ ተፋስስ ላይ የምትሰራቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከአፈር መሸርሸር እና ግድቦችን በደለል መሞላት ከመጠበቅ ባሻገር በአየር ንብረት ለውጥ እና በወንዝና ውሃ አጠቃም ላይ ለሚፈጠሩ ቀጣናዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሁነኛ መፍትሄ ይሆናሉ ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ እየሰራች ያለችው የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ስራ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸው፤ስራዎቿን በጥናት አስደግፋ ለዓለም አቀፍ ባለድርሻዎች ማቅረብና አቅም መፍጠር እንዳለባት ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት መዘዞች ሰለባ መሆኗን ጠቅሰው፤ በአንድ በኩል በሳይንሳዊ ጥናቶች ስራዎቿን ማሳወቅ፤ በሌላ በኩል ለስራዎቿ ድጋፍ ለማግኘት መደራደር እንደሚገባት ነው ያነሱት።

ለሰው ልጆች ሕልውና ስጋት ለሆነው አየር ንብረት ለውጥ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ላይ ለመድረስ በተባበሩት መንግስታት አይነተ ብዙ መድረኮች ይደረጋሉ።

በዘርፉ በጉልህ ከሚጠቀሱ ጉባዔዎች መካከል አንዱ ከ100 በላይ የዓለም አገራት መሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ወይም ‘ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ’ ከነገ በስትያ በግብጽ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም