ኢትዮጵያ ለኔልሰን ማንዴላ ልዩ ክብርና ቦታ እንዳላት ተገለጸ

46
ኒዮርክ መስከረም 15/2011 ኢትዮጵያ ለኔልሰን ማንዴላ ልዩ ክብርና ቦታ እንዳላት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ተናገሩ። ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህን ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የኔልሰን ማንዴላ (ማዲባ) 100ኛ ዓመት የልደት በዓልን ለማክበር በኒውዮርክ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ነው ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በተመራውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ በመካፈል ላይ በሚገኘው ልኡክ ጋር በውይይቱ በመካፈል ላይ የሚገኙ ሲሆን ከውይይቱ ጎን ለጎን ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የአፍሪካ ብርቅዬ ልጅ እንዲሁም የዓለም የዲፕሎማሲና የመሪነት ፈርጥ እንደነበሩ ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በተለይም "ኢትዮጵያ ለኔልሰን ማንዴላ ልዩ ክብርና ቦታ እንዳላት" ገልጸዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው ማንዴላ ከኢትዮጵያ ጋር ልዩና ጠንካራ ቁርኝት እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ የማዲባ ህይወትና አሻራዎች የ73ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ጠቅላላ ጉባዔ አካል ሆነው በመታወስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የማንዴላ መታሰቢያ ሀውልትም በትላንትናው እለት በይፋ ተመርቆ ኒውዮርክ በሚገኘው የተ.መ.ድ አዳራሽ ውስጥ በክብር መቆሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መግለጫ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም